ሃዋሳ በከፍተኛ የውሃ ችግር ተጠቅታለች ተባለ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 06 ቀን 2010 ዓ/ም) የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት የአዋሳ ህዝብ ንጹህ ውሃ ያገኛል ብሎ መናገር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። በ15 ቀናት ውስጥ ለአንድ ወይም ለ2 ቀናት ለተወሰኑ ሰዓታት ውሃ ካገኙ በሁዋላ መልሶ እንደሚሄድባቸው የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ ሰሞኑን ደግሞ ሴቶች የወንዝ ውሃ ፍለጋ ከ3 እስከ 4 ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ነው።
በአህያ ጭነው ውሃ ከሚያመጡ ነጋዴዎች ላይ 20 ሊትር የሚይዘውን ጀሪካን ከ13 እስከ 15 ብር እያወጡ እንደሚገዙ የሚገልጹት ነዋሪዎች፣ በተለይ በኮንዶሚኒየም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለከፍተኛ ስቃይ ተዳርገዋል። በኮንዶሚኒየም ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለመጸዳጃ ቤታቸው የሚሆን ውሃ ማግኘት ባለመቻላቸው መኖሪያ ቤታቸው የሚፈጠረው መጥፎ ጠረን ለበሽታ እየዳረጋቸው ነው።
ነዋሪዎቹ በከተማው ውሃ ወለድ በሽታ ከመከሰቱ በፊት መዘጋጃው መፍትሄ እንዲፈልግላቸው እየጠየቁ ነው።