ሚያዚያ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2004 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት አገሪቱ የተለመደውን ቡና፣ቆዳና ሌጦ፣ጥራጥሬ፣ጫት እና የመሣሰሉትን ለዓለም አቀፉ ገበያ በማቅረብ ከተገኘው ገቢ ይልቅ በሃዋላ የሚገኘው የውጪ ምንዛሪ የተሻለ ደረጃ አገኘ፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው በተጠቀሰው ግዜ ከወጪ ንግድ 1.6 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተገኘ ሲሆን በውጪ አገር ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ከላኩት ሃዋላ 1.74 ቢሊየን ዶላር ተገኝቷል፡፡
የወጪ ምርቶች ንግድ እና ከሃዋላ የተገኘው እያንዳንዳቸው ከአምና ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸሩ በ20 በመቶ ብልጫ አሳይተዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከሁለት ሚሊየን በላይ ይገመታል፡፡ በሌላም በኩል በበጀት ዓመቱ ሰባት ወራት የገቢ ንግዱ ከወጪ ንግዱ ጋር ባለመጣጣሙ የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት አምና በተመሣሣይ ወቅት ከነበረበት የ3.4 ቢሊየን ዶላር ወደ 4.5 ቢሊየን ዶላር አሻቅቧል፡፡በዚሁ ወቅት አገሪቱ ከገቢ ንግዱ ያገኘችው 6 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ሸቀጦችን ከውጪ አገር ሸምቶ ለማስገባት የወጣው ወጪ በሰባት ወራቱ 28 በመቶ አድጓል፡፡
የሀዋላ ገቢ ከኤክስፖርት መብለጡ ዲያስፖራው ለአገሪቱን ኢኮኖሚ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን የሚያመለክት ነው። ዲያስፖራው ይህን እምቅ ሀይሉን ተጠቅሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ ፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና የህግ ልእልና እንዲኖር ለማድረግ አለመቻሉን ምሁራን ይናገራሉ። የአቶ መለስ መንግስት ከዲያስፖራው የሚያገኘው ከፍተኛ ገቢ ለተወሰነ ወራት ቢቋረጥ፣ ወይም ዲያስፖራው ገንዘብ የሚልክበትን ስርአት ቢቀይር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ፦”ዳያስፖራውም ብሶት ፤ እኛም ብሶት ካወራን ለውጥ አናመጣም” ሲሉ ተናገሩ።
በልማት ለመሰማራት ብለው ከውጪ አገራት ወደ አገር ቤት ካቀኑ ኢትዮጵያውያን ተስፋ የመቁረጥ ብሶት፣ምሬትና ሮሮ ሢሰማ የዋለው፤ለዳያስፖራው መረጃ ለመስጠትና ችግሮችን ተቀራርቦ በመነጋገር መፍትሔ ለማፈላለግ ተብሎ ሰሞኑን በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ነው።
በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በተካሄደውና በውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተመራው በዚሁ የውይይት መድረክ፣ የዳያስፖራው አባላት የፍትሕ እጦት፣ ሙስናና የቢሮክራሲ ችግሮች በአገሪቷ ተንሰራፍተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
“መንግሥት ሁሌም ችግራችሁን ተናገሩ ይላል፡፡ ሆኖም ችግሮች ሲፈቱ አይታይም፡፡ የዳያስፖራው ቢሮ ቢቋቋምም፤ አጥጋቢ መልስ አናገኝም” ሲሉ የመድረኩ ተሳታፊዎች ብሶታቸውን እንዳሰሙ የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።
በተለይ በኢሉባቦር አካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን የገለጹ የስብሰባው ተካፋይ፣ “አገራችን ገብተን እንድንሠራ ጩኸት ይጮኻል፤ ሆኖም አገራችን ስንገባ የምናየው ሌላ ነው፡፡ ገብተን ከምንሠራው፤ ገብተው ጥለው የሄዱት ይበልጣሉ” ብለዋል።
ኢሉባቦር ላይ የእርሻ ሥራ ቢጀምሩም ፦” ውጣ፣ አለበለዚያ እንገልሃለን “ መባላቸውን የጠቆሙት እኚሁ ግለሰብ፤” የቡና እርሻችን ላይ እሳት ተለቆብናል፡፡ ከብት በእርሻ ላይ ይለቀቃል፡፡ ያልደረስንበት ቦታ የለም” ሲሉ ምሬታቸውን አሰምተዋል።
“የዳያስፖራው ቢሮ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው፡፡ ለመተንፈስ ያህል እንተንፍስ እንጂ መፍትሔ የለም፤” ሲሉም ለልማት ወደ አገር ቤት የሚሄዱ ዲያስፖራዎችን ለመርዳት ተቋቁሟል የተባለው ቢሮ የፌዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግስት ሲቪል ሰርቪሱን አንዴ በቢ.ፒ. አር ሌላ ጊዜ ደግሞ በግምገማ እያያሻለው እንደሚገኝ ቢለፍፍም፤ የዲያስፖራ አባላቱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ፦”ደንበኛ ንጉሥ ነው የሚለው አሠራር ቀርቶ፤ ሠራተኛው ንጉሥ የሆነበት አሠራር መንሰራፋቱን ነው በስብሰባው ያንጸባረቁት።
በዚሁ ስብሰባ ላይ ፦ “ወደ አገራችን ስንገባ መንገላታቱ የሚጀምረው ከጉምሩክ ነው፤” ያሉም ተሳታፊዎች ተሰምተዋል፡፡
የታክስ ክፈል አትክፍል ክርክር ብቻ ሳይሆን፤ ታክስ ቢከፈልም ጉዳዮች በፍጥነት እንደማያልቁና የአሠራር ክፍተቱ የጐላና የሚያማርር እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ከፈረንሳይ የመጡት ወይዘሮ ገነት አየለ፦”“የሊዝ አዋጁ ከወጣ በኋላ ሕዝቡን ለምን ማወያየት አስፈለገ? አወያይታችሁስ ያገኛችሁትን ግብዓት ታካትታላችሁ? አዋጁን ትሽራላችሁ? አወያይታችሁ ምን አደረጋችሁ?”በማለት ሲናገሩ የማያቋርጥ ጭብጨባ አጅቧቸዋል።
የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ መኩርያ ኃይሌ በበኩላቸው ቤቱን በስፋት ላስጨበጨበው የሊዝ አዋጁ ጥያቄ በመንግሥት በኩል ክፍተትና ውስንነት እንደነበረ አምነዋል፡፡
“በሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮች ከብቃትና ከአመለካከት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ይህንንም በተመለከተ ሥልጠና እየተሰጠ ግምገማም እየተደረገ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ በአሠራሩ ላይም አዲስ ሥርዓት ተዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ታቅዷል” ብለዋል- መድረኩን ሲመሩ የነበሩት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣የከተማ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሀይሌ መኩሪያ እና የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥው አቶ ዮሐንስ አያሌው።
ሲቪል ሰርቪሱ በሚገባ አገልግሎት እንደማይሰጥና የመንግሥት ሠራተኛው ንጉሥ እንጂ አገልጋይ እንዳልሆነ ለተነሳው ጥያቄ፣ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ ፦”ይህ ሊሆን እንደሚችልና ሲቪል ሰርቪሱ በሚሰጠው አገልግሎት ጥራት ላይ ክፍተት እንዳለ ይታወቃል” ብለዋል፡፡
‹‹ይሁንና ከደርግ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ለውጥ አስመዝግበናል። ይህንን ለውጥ ያስመዘገብነው ትንሽም ቢሆን ስለሠራን ነው” ሲሉ አክለዋል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለሚነሱባቸው ጉድለቶችና ጥፋቶች በተደጋጋሚ ደርግን እንደማነፃጸሪያ በመጥቀስ የተሻልን ነን እንደሚሉ ይታወቃል።
“መድረኩ የተዘጋጀው ብሶት ሰምተን ብሶት መለዋወጫ ለማድረግ አይደለም፡፡ ተወያይተን በጋራ ችግሩን ለመፍታት ነው፤ እናንተም ብሶት፤እኛም ብሶት ካወራን ለውጥ አናመጣም” ሲሉም አቶ ሀይለማርያም ተወያዮቹን ሸንቆጥ አድርገዋቸዋል።
የኢህአዴግ መንግስት በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አመቺ የ ኢንቨስትመንት ዕድል እንደተፈጠረ የሚናገረውን አምነው ለዓመታት ያጠራቀሙትን ጥሪታቸውን ይዘው ለሥራ ወደ አገር ቤት ካቀኑት መካከል ብዙዎቹ በ አጭር ጊዜ ውስጥ ባዶ እጃቸውን ቀርተው ሲያለቅሱና ብሶታቸውን ሲያሰሙ ይደመጣሉ።
ለዲያስፖራው ተመቻችተው ከነበሩት ዕድሎች አንዱ መኪና እና ዕቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የሚል ነበር። ይህ ግን በአሁኑ ጊዜ ተከልክሏል።የስብሰባው ተሳታፊዎች ፦”ይህ ዕድል ለምን ተከለከለ?” በማለት ጠይቀው ነበር።
አቶ ኃይለ ማርያም ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት የጀመሩት፦“እናንተ ተሰብስባችሁ እዚህ ስለተወያያችሁ እናንተ ብቻ ኢትዮጵያዊ አይደላችሁም”በማለት ነው።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም፦”ሁለት ሚሊዮን ዳያስፖራ ቢኖር ፤79 ሚሊዮኑ ኢትዮጵያዊ ፤አገር ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ ሁሉም በመኪና መጠቀም ይፈልጋል፡፡ ይህ ቅንጦትም አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው መኪና ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የመጠየቅ መብት አለው፡፡ አሠራሩ ፍትሐዊ መሆን ስላለበት ፤መንግሥት ተሳስቶ የወሰነውን የቀረጥ ነፃ መብት ለሁሉም መዝጋት ነበረበትና ዘግቷል”በማለት እቅጩን ነግረዋቸዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide