ኢሳት (ጥር 6 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳባቸውን በነጻነት በሚገልጹ አካላት ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆም የአሜሪካ መንግስት አሳሰበ።
በወቅታዊ የኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ዙሪያ በድጋሚ መግለጫን ያወጣው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተቃዋሚ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በጋዜጠኞች ላይ የሚወሰደውን እርምጃ አሳስቦት እንደሚገኝ ገልጿል።
እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም ፖለቲካዊ ችግሮችን ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን መፍትሄን ለማፈላለግ በሚያድርጉ ጥረቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድሩ የአሜሪካ መንግስት አስታውቋል።
መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከህበረተሰቡ ጋር የጋራ ምክክር አካሄዳለሁ ሲል የገለፀው አቋም እንደሚደግፍ የገለጸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውይይቱ ውጤታማ ትርጉም ያለው እንዲሆን ፓርቲዎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለጽ እንደሚኖርባቸው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሃገሪቱ የተደነገጉ ህጎችን በሚከበር ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እንዲሁም የመሰባሰብና በነጻነት የመናገር መብቶች እንዲያከብርም አሜሪካ በድጋሚ አሳስባለች።
መብታቸውን ተጠቅመው ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ለእስር የተደረጉ ጋዜጠኞችና የፓርቲ አመራሮችም በአስቸኳይ እንዲፈቱ አሜሪካ ጠይቃለች።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ አሜሪካ ባለፈው ወር ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥታ እንደነበር ይታወሳል።
አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትም የአውሮፓ ህብረትና የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ዝምታቸውን በመስበር በሃገሪቱ እየተካሄደ ስላለው ግድያና እስራት ምላሽን እንዲሰጡ ዘመቻ ከፍተው ይገኛል።
ይህንኑ አለም-አቀፍ ዘመቻም ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት በተያዘው ሳምንት ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በብራሰልስ ምክክር ማካሄዱ ይታወቃል።
በዝግ ተካሄዷል በተባለው በዚሁ ውይይት የህብረቱ ባለስልጣናት በኦሮሚያ ክልል ስላለው ተቃውሞ ማብራሪያ መጠየቃቸውንና ሰፊ ውይይት ማካሄዱም ተገልጿል።