ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አለም አቀፍ ሆቴል የሆነውን ሂልተን አዲስ ሲያስተዳድር የቆየው መንግስት ሆቴሉ በጨረታ እንዲሸጥ ወሰነ።
በአጼ ሃይለ-ስላሴ መንግስት ዘመን ስራውን የጀመረው ሆቴል ለጨረታ እንዲቀርብ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ከሂልተን አዲስ የቦርድ ዳይሬክተሮች ጋር ሰሞኑን ምክክር ማካሄዱንና ለጨረታው ሽያጭ ዝግጅት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ መስጠቱን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል። እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1969 አም ስራውን የጀመረውን ይህንኑ ሆቴል ለማስተዳደር መንግስት ከሂልተን ወልድዋይድ (አለም አቀፍ) ኩባንያ ጋር የ50 አመት ስምምነት የነበረው ሲሆን፣ ይኸው ስምምነት በየአስር አመቱ ሲታደስ መቆየቱ ታውቋል።
ይሁንና በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የመጨረሻ ውል ፍጻሜው ሲቀርብ ሂልተን አዲስ በጨረታ እንዲሸጥ በመንግስት በኩል ውሳኔ መድረሱን ጋዜጣው አስነብቧል። ለበርካታ አመታት በቆየው በዚሁ ስምምነት ሂልተን ወርልድዋይድ ከሂልተን አዲስ የ20 በመቶ ከገቢ ትርፍ ጥቅም ተጋሪ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ሆቴሉ ለጨረታ ሲቀርብ ሂልተን ወርልድዋይድ ሆቴሉን ለመግዛት ዋነኛ ተጫራች ሆኖ ለመቅረብ ፍላጎት አሳይቷል።
በልዩ ፈቃድ (ፍራንቻይዝ) ሲተዳደር የቆየው ሂልተን አዲስ ባለ 12 ፎቅ የመኝታ እና በአዲስ አበባ ከተማ 400 የመኝታ ክፍሎችን በመያዝ ብቸኛው ሆቴል መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።
ሆቴሉን ሲያስተዳድር የቆየው መንግስት ሂልተን አዲስ በተመሳሳይ ስም ሌላ ሆቴል እንዳይከፍት አድርጎ የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡ በተካሄደ የደረጃ አሰጣጥ ሂልተን አዲስ የባለ ሶስት ኮከብ ደረጃ እንደተሰጠው ታውቋል። ይሁንና፣ የሆቴል ባለሙያዎች በሆቴሉ የነበረው የማኔጅመንት ችግር እንዲሁም ደረጃውን ለመስጠት በአጭር ጊዜ የተካሄደ ስራ ሆቴሉ የሚመጥነው ደረጃ እንዳልተሰጠው ገልጸዋል።
በሂልተን አዲስ ሆቴል በማኔጅመንቱ ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት ችግሮች እንዳሉ የሚናገሩት የዘርፉ ባለሙያ አቶ ፍሰሃ አስረስ ሆቴሉ ባለ አራት ኮከብ ደረጃ ከተሰጣቸው ሆቴሎች የተሻለ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ይሁንና በማኔጅመንት በኩል ያሉ የአገልግሎት ችግሮች እና የጥገና ስራዎች በደረጃ አሰጣቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ባለሙያዎች ተናግረዋል። ከ10 አመት በፊት ሂልተን አለም አቀፍ ሆቴሉን 280 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የሚያወጣ እድሳት እንደሚፈልግ ቢገልፅም፣ መንግስት ሃሳቡን ውድቅ እንዳደረገው ለመረዳት ተችሏል።
ከጥቂት አመታት በፊት የሂልተን አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሆቴሉ በጨረታ እንዳይሸጥ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ ሆቴሉ በጨረታ እንዲሸጥ ውሳኔ አስተላልፏል።
ከኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ የተሰጠው ይሁንታ ተከትሎ ሰንሻይን ግሩፕ ከሂልተን አለም አቀፍ ጋር ስምምነት በማድረግ በሃዋሳ ከተማ ሂልተን ሃዋሳ ለመክፈት የዲዛይን ስራ እያካሄደ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል። ከ60 ሺ ስኩዌር ሜትር በላይ ይዞታ ያለው ሂልተን አዲስ በምን ያህል መነሻ ገንዝበ ለጨረታ እንደሚቀርብ የተገለጸ ነገር የለም።