ሂልተን ሆቴል ሊሸጥ ነው

ሚያዝያ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የነበረውን ሒልተን ሆቴል ሊሸጥ መሆኑን ሳምንታዊው ሪፖርተር ዘግቧል።
እንደ ጋዜጣው ዘገባ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የሂልተንን ሽያጭ አስመልክቶ ከሦስት ወራት በኋላ ጨረታ ያወጣል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዚህ ጨረታ ለመሳተፍ ከአሥርያላነሱ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየተጠባበቁ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሂልተን አዲስ አበባን ለመግዛት ፍላጎት ካሳዩ ኩባንያዎች መካከል ሰንሻይን ግሩፕ፣ መቀመጫቸውን ሆንግ ኮንግና ዱባይ ያደረጉት ሻንግሪላና አል ባዋርዲ ኢንቨስትመንትስ ይገኙበታል፡፡
ሰንሻይን ግሩፕ መስቀል አደባባይ አካባቢ ማርዮት ሆቴልን እንዲሁም በዚሁ ዓለም አቀፍ የንግድ ስያሜ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ተጨማሪ ሆቴል እየገነባ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪምበሐዋሳ በሒልተን ሆቴል ስያሜ የሚተዳደር የሆቴል ፕሮጀክት ነድፏል፡፡
የመጀመሪያውን ሆቴል በሲንጋፖር በመገንባት ወደ ሆቴልና ሪዞርት ቢዝነስ የገባው ሻንግሪላ ደግሞ በበርካታ አገሮች 99 ሆቴሎችንና ሪዞርቶችን ያስተዳድራል፡፡ ይኼ መቀመጫውን ሆንግኮንግ ያደረገው ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ሒልተን ሆቴልን ለመግዛት ጥያቄ ማቅረቡን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ሂልተንን ለመግዛት ፍላጎት ያሳዬው ሦስተኛው ኩባንያ አል ባዋርዲ ኢንቨስትመንትስ የተሰኘ ነው፡፡ ይኼ ኩባንያ ቀደም ሲል “አልካሪፊ ሆቴል ኢትዮጵያ”የሚባል ኩባንያ መስቀል አደባባይየገነባቸውን ሁለት የሆቴል ፕሮጀክቶች በ25 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ኢትዮጵያ የገባ ነው፡፡
ላለፉት 50 ዓመታት ሆቴሉን ሲያስተዳደር የቆየው ሒልተን ፤ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የገባው ውል ሊጠናቀቅ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ ብቻ እንደቀረው ታውቋል።በዓጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ባለ 12 ወለል ከፍታ እንዲኖረው ተደርጎ በላሊበላ ቅርፅ ውብ ሆኖ የተገነባው ሒልተን አዲስ አበባ፤ በ60 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡
ይሁንና ሙሉ በሙሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ንብረት የሆነው ሒልተን ሆቴል በቂ እድሳት ሳይደረግለት በመቅረቱ ፣ እንዲሁም የማብሰያና የእንግዳ ክፍሎች አያያዝ ላይ በቅርቡ በተባበሩትመንግሥታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባለሙያዎች በተካሄደ ምዘና አነስተኛ ነጥብ በማግኘቱ፣ ባለሦስት ኮከብ ሆኖ መመደቡ ይታወሳል፡፡