ሁለት የነጻነት ታጋዮች አራት ወታደሮችን ገድለው ተሰው

ታኅሣሥ ፲ (አሥር)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በኮሚቴ አባልነት ተመርጦ ሲንቀሳቀስ እና የነጻነት ተጋድሎ ሲያደርግ የነበረው  አቶ ዘውዱ ገ/እግዚአብሄርና ሌላው ጓደኛው አቶ ሙላው ከበደ ታህሳስ 9 ቀን 2009 ዓም መተማ ቁጥር 2 በሚባለው አካባቢ  እነሱን ለመያዝ ከመጡ ወታደሮች ጋር ተፋልመው 4 ወታደሮችን ገድለው  ተሰውተዋል። ከኮርመር የተነሱት ወታደሮች፣ ታጋዮቹን በቀላሉ እንይዛለን ብለው ቢሄዱም ያልጠበቁት ተኩስ ተከፍቶባቸዋል።

በደረሰው ጉዳት የተበሳጩት ወታደሮች በአካባቢው በእርሻ ስራ ላይ የተሰማራውን ባለሀብት ይልማ ፈረደን አፍነው ወስደዋል። ወጣት ሙላው ከበደ  ከባህርዳር ዩነቨርስቲ በኢኮኖሚክስ ተመርቆ በሁመራ ንግድና እንድስትሪ ተመድቦ ሲሰራ ቆይቶ ከብሄሩ ጋር በተያያዘ ከስራው እንዲለቅ ከተደረገ በሁዋላ፣ መብቱን ለማስከበር ሲታገል ቆይቷል።

ድርጊቱ ያበሳጫው በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎች በአገዛዙ ወታደሮች ላይ የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።