ሁለት ኢትዮጵያውያን በካይሮ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ጽ/ቤት በራፍ ላይ ራሳቸውን አቃጠሉ

ኢሳት (ሃምሌ 14 ፥ 2008)

ሁለት ኢትዮጵያውያን ካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በራፍ ራሳቸውን አቃጠሉ። በቅርቡ ኦሮሚያ ከተካሄደው መጠነ ሰፊ ግድያና እስራት ሸሽተው ግብጽ መድረሳቸው የተገለጸው እነዚህ ሁለት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ራሳቸውን ያቃጠሉት በተቃውሞ መሆኑን ተመልክቷል።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በማቃጠል ተቃውሟቸውን የገለጹት የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የካይሮ ቢሮ የስደተኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ በማድረጉ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።

በግብፅ ካይሮ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በርካታ ኢትዮጵያውያን የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ በማድረጉ ብዙዎች በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚያደርጉት ጉዞ ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል።

ለጊዜው ስማቸው ያልታወቀው ኢትዮጵያውያን መቃጠላቸውን ተከትሎ ፖሊስ በስፍራው የደረሰ ሲሆን፣ ኦ ኤም ኤን (Oromo Media Network) ይፋ ካደረገው ቪዲዮ መረዳት እንደተቻለው በአካባቢው ጩኸት ይሰማ ነበር።

ራሳቸውን ካቃጠሉት ኢትዮጵያውያን አንዱ ቆዳው ተለብልቦ የታየ ሲሆን፣ የሁለቱም ጤንነት አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ አልተቻለም።