ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-ሀዲያ ውስጥ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በዞኑ መስተዳድር መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ተከትሎ በተቀሰቀሰ ግጭት ሁለት ፖሊሶችና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ምሩቃን ተማሪዎች መጎዳታቸው ተገለፀ።
እንደ ፍኖተ-ነፃነት ዘገባ ግጭቱ ሊፈጠር የቻለው በሀዲያ ዞን ሆሣዕና ከተማ የሚገኙ በተለያየ ዓመት ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው ሥራ ያጡ ወጣቶች ለዞኑ መስተዳደር ጥያቄ በማንሳታቸው ታስረው በመደብደባቸው ነው።
ምንጮቹን በመጥቀስ ጋዜጣው እንደዘገበው፤ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው 2 ዓመትና ከዚያ በላይ ሥራ አጥ የሆኑ 429 ወጣቶች የዞኑ መስተዳደር መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ባለፈው ታህሣሥ 19 ቀን ጥያቄ በማንሳታቸው፤ 8ቱ ተወካዮቻቸው በመስተዳደሩ ቢሮ ለረጅም ሰዓታት ታግተው ተደብድበዋል፡፡
ቀሪዎቹ ድንገት በመጡ በዞኑ ፖሊሶች ከመስተዳደሩ ቢሮ እንዲወጡ ትዕዛዝ ሢሰጣቸው፦ “ተወካዮቻችንን ጥለን አንሄድም፣ ምላሽም እንፈልጋለን” በማለታቸው ሳቢያ በተፈጠረ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወጣቶችና 2 ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተመልክቷል
በአሁኑ ጊዜ 8ቱን ተወካዮች ጨምሮ 11 ምሩቃን ተማሪዎች ታስረው ይገኛሉ፡፡
ስለጉዳዩ የተጠየቁት የሀዲያ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኮማንደር አዲሴ ፈይሳ 11 ወጣቶች መታሰራቸውን እና ሁለት ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ያመኑ ሲሆን፤ የተደበደቡ ወጣቶች ግን እንደሌሉ ለማስተባበል ሞክረዋል።
በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በደቡብ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ የመብትና የነፃነት ትግሉ እየተቀጣጠለ መምጣቱ፤ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ትኩሳት በሚከታተሉ ታዛቢዎች ዘንድ አድናቆትን እየፈጠረ ይገኛል።