ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነገ ዋሽንግተን ዲሲ ይገባሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 18/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነገ ሐሙስ ማለዳ ዋሽንግተን ዲሲ ይገባሉ ተባለ።

የፊታችን ቅዳሜ ከ25ሺ ከሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ጋር በዋሽንግተን ሲዲው ኮንቬንሽን ሴንተር እንደሚመክሩም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ እለት ምሽት ላይ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከተመረጡ 1 ሺ 500 ኢትዮጵያውያን ጋር የሚወያዩበት ሌላ መርሃ ግብርም ተይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዋሽንግተን ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች፣ከምሁራንና ከሌሎች ወገኖች ጋር በጠባብ መድረኮች እንደሚወያዩም ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።

በቀጣዩ ቀን እሁድ ወደ ምዕራቡ የአሜሪካ ክስል ሎስ አንጀለስ በመጓዝ በካሊፎሪያና በአጎራባች ግዛቶች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በትልቅ መድረክ ውይይት ያደርጋሉ ተብሏል።

ሰኞ ወደ ሚኒሶታ የሚያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚኒያፖሊስ ከተማ በሚኒሶታና አካባቢዋ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር እንደሚወያዩ የወጣው መርሃ ግብር አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር የሚያደርጉት ውይይት “ግንቡን እናፍርስ ድልድዩንም እንገንባ”የሚል መሪ ቃል የያዘ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።