የዚምባቡዌው ሮበርት ሙጋቤ 150 ሺህ ዶላር ተሰረቁ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 11/2011)ከቀድሞ የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሻንጣ 150 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሰረቁ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ ገንዘቡን እንደሰረቁና በገንዘቡም ተሽከርካሪ ቤትና ከብቶች እንደገዙበት አቃቤህግ አስታውቋል።

ከሌቦቹ ውስጥ የሮበርት ሙጋቤ የቅርብ ዘመድ እንደሚገኙበትም ታውቋል።

ዚምባቡዌን ለ37 ዓመታት ያህል የገዙትና በወታደሮች አስገዳጅነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ስልጣናቸውን የለቀቁት የ94 ዓመቱ አዛውንት ሮበርት ሙጋቤ 150 ሺህ ዶላር የተሰረቀው ከገጠር መኖሪያቸው ነው።

ይህ የገጠር መኖሪያቸው ከርዕሰ መዲናዋ ሃራሬ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል።

የሮበርት ሙጋቤ የገጠር መኖሪያ ቤት ቁልፍ ያላት ዘመዳቸው ከቤት ሰራተኞች ጋር ተመሳጥራ ገንዘቡን እንደሰረቀችም ተመልክቷል።

150 ሺህ ዶላር ሰርቀዋል በሚል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ከቀረቡት ሶስት ግለሰቦች ውስጥ ሁለቱ የቤት ሰራተኞች በሰረቁት ገንዘብ ንብረት እንደገዙበትም ተደርሶበታል።

አልጀዚራ እንደዘገበው አንደኛዋ ሰራተኛ ቶዮታ ካምሪ መኪና እና መኖሪያ ቤት ስትገዛ ሌላኛዋ ሰራተኛ ደግሞ ሆንዳ መኪና እንዲሁም ግመልና አሳማን ጨምሮ የቤት እንስሳትን ገዝታ ተገኝታለች።

3ቱ ተጠርጣሪዎቹ ከሳምሶናይት ውስጥ በሰረቁት 150 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም በዋስ ተፈተው ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ ተፈቅዶላቸዋል።

ዚምባቡዌ ነጻነቷን ካገኘችበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1980 ጀምሮ ለ37 ዓመታት በመሪነት ስልጣን የቆዩት ዶክተር ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በ2017 ተገደው ስልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን የሃገሪቱ የነጻነት አርበኛ በመሆናቸውም ተገቢው ክብር አልተነፈጋቸውም።

ከዕድሜና ከጤና ጋር በተያያዘ በወጉ ለመራመድ የሚቸገሩ ሲሆን ለህክምና ወደ ሲንጋፖር በመመላለስ ላይ መሆናቸውም ታውቋል።