(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2011) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረ ገጹ ለተጠቀመው የተሳሳተ ካርታ ይቅርታ ጠየቀ።
ሶማሊያን የኢትዮጵያ አካል አድርጎ በወጣው ካርታ በመላው ዓለም የሚገኙ ሶማሊያውያን ተቃውሞ አሰምተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የተሳሳተውን የአፍሪካ ካርታ ከድረገጹ እንዲወርድ መደረጉን ገልጸው ሁኔታው እንዴት እንደተከሰተ በማጣራት ላይ ነን ብለዋል።
ካርታው ከሶማሊያ ሌላ የሌሎች የአፍሪካ ሀገራትንም ድንበሮች በተሳሳተ መልኩ የሚያሳይ በመሆኑ ውዝግቡን አጠናክሮታል።
አቶ ነቢያት ካርታውን በሚኒስቴሩ መስሪያ ቤት ድረገጽ ላይ ማን እንደለጠፈ አናውቅም ማለታቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ባለፈው ቅዳሜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረገጽ ላይ የወጣው ካርታ ሶማሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቅሏታል።
ሶማሌላንድን ደግሞ በሉአላዊ ሀገርነት ድንበርና ግዛት ያላት አድርጎ ያሳያታል።
ደቡብ ሱዳን በካርታው ላይ የለችም። ሁለቱን ኮንጎዎች ተቀላቅለው በአንድ ሀገርነት ቆመዋል።
ስዋዚላንድና ሌሴቶም ካርታው ላይ አይታዩም። ኢኳቴሪያል ጊኒም እንዲሁ።
ካርታው ከፍተኛ ውዝግብ የፈጠረው የዚያኑ ዕለት የሶማሊያ አክቲቪስቶች በቲውተር ዘመቻ መክፈታቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካን ሬዲዮ የሶምሊኛ ፕሮግራም ጋዜጠኛ ከዚህ ካርታ ላይ ሶማሊያ የት እንዳለች ሊያሳየኝ የሚችል ማን ነው? የሚል ጥያቄ አንስቶ በቲውተር ላይ የተሳሳተውን ካርታ በመለጠፍ የጻፈው የቲውተር መልዕክት በመላው ዓለም የሶማሊያ ተወላጆችን ትኩረት በመሳቡ ተቃውሞ መነሳቱን ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ስህተቱ እንዴት እንደተፈጠረ የሚታወቅ ነገር የለም ብለዋል።
ወዲያውኑ ካርታው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ መነሳቱን ነው አቶ ነቢያት ለጋዜጠኞች የገለጹት።
በዚህም ለተፈጸመው ስህተት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይቅርታ ይጠይቃል ብለዋል።
በተሳሳተው ካርታ ምትክ ትክክለኛው እንዲወጣ ተደርጓል ያሉት አቶ ነቢያት ጌታቸው የተሳሳተው ምስል በድረ ገጹ ላይ በማን እና እንዴት እንደወጣ በሚመለከተው አካል ማጣራት እየተደረገበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ካርታው ከየት እንደተገኘና ማን ድረ ገጹ ላይ እንደለጠፈው ገና አልታወቀም ብለዋል አቶ ነቢያት።
መስሪያ ቤታቸው ካርታ የሚጠቀመው ከኢትጵያ ካርታ ሥራዎች ኤጀንሲ መሆኑን የገለጹት አቶ ነቢያት ይህኛውን የተሳሳተውን ለምን ዓላማ እንደተለጠፈ እያጣራን ነው ሲሉ መግለጻቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ጉዳዩንም አጣርተን ርምጃ እንወስዳለን ብለዋል።