የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት፣ የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት ወደ ኢትዮጵያ ሊጀምር ነው።

ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ፣

ሚያዚያ 1 ቀን 2002 ዓም
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት የተለያዩ፣ የዜና፣ የውይይት፣ ጥናታዊ፣ የመዝናኛ ፣ የስፖርት ፕሮግራሞቹን፣ በቀጥታ ወደ
ኢትዮጵያ እና ወደ ሌሎች የአለም ክፍሎች በኤፕሪል መጭረሻ ማሰራጨት ይጀምራል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት ያቋቋምን አካላት ኢትዮጵያ ሀገራችን እና ህዝቧ አሁን ለሚገኙበት እጅግ አስቸጋሪ እና
ውስብስብ ሁኔታ ውስጥ እንዲደርሱ ከአደረጓቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ እና ዋናው፣ ለረጅም ዘመን ህዝቡ ስለ እራሱ እና በጋራ
ስለሚኖርባት ሀገር ስለሚገኙበት ሁኔታ፣ ትክከለኛውን መረጃ በአይነትም ሆነ በመጠን ማግኘት አለመቻሉ ነው ብለን እናምናለን።
ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ዛሬ ለሚገኙበት እጂግ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ችግሮች በተመለከተ መፍትሄ መፈለግ አለብን ብሎ ከልቡ
የሚያስብ ዜጋ በሙሉ፣ ህዝብ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት፣ በአገኛቸውም መረጃዎች ላይ ተመስርቶ በጋራ
በመምከር፣ የጋራ መፍተሄ ማፈላለግ፣ ብሎም ለመፍትሄው ተግባራዊነት በጋር ለመንቀሳቀስ የሚችለው፣ ነጻ እና አስተማማኝ የመረጃ
ምንጭ ሲኖር ብቻ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት የህዝብ ዓይን እና ጆሮ፣ የመገናኛ ብዙሀን በመሆን፣ አስተማማኝ ነጻ እና ገለልተኛ
መረጃዎችን በማቅረብ፣ ለችግሮቻችን መፍተሄ ለመፈለግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን አስተዋጽዖ ለማድረግ ዝግጁ ሆኖ ቀርቧል።
የጋራ ችግሮቻችን መፍትሄ ያገኙ ዘንድ ከጋራ ጥረት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም ። በጋራ ጥረት ለማድረግ ደግሞ በጋራ ሊያስማሙን
የሚችሉ ጉዳዮች ሊኖሩን ይገባል። የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት የሚቀርቡ ፕሮጋራሞች በሙሉ ሁላችንንም በጋራ
ሊያስማሙን ከሚችሉት የእውነት፣ የሚዛናዊነት፣ የግጽነት እና የተጠያቂነት መመዘኛዎችን ያሟሉ መሆን ይኖርባቸዋል። እነዚህን
መዘኛዎች ሳያሟሉ ቢቀሩ ግን፣ ሀገራችንን እና ህዝቧን ለዘመናት ተብትቦ ወደ አዘቅት እያወረደን ካለው የጥቂት ግለሰቦች ወይም
ቡድኖች ጉዳይ ማስተናገጃ መድረክ ከመሆን አዙሪት መውጣት ስለማንችል፣ ጥረታችን ሁሉ ከንቱ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎትን ያቋቋምን ወገኖች ይህንን ከፍተኛ የግንዛቤ፣ የእቅድ፣ የገንዘብ እና የማቴሪያል፣ ከሁሉም
በላይ ደግሞ ይቻላል የሚል የመንፈስ ጽናት፣ የሚጠይቅ ጥረት፣ በጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከታሰበለት ግብ ማድረስ ይቻላል
የሚል እምነት የለንም። ይህ ጥረት በተወሰኑ ሰዎች ይጀመር እንጂ፣ የታሰበለትን ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ ሁላችንንም በምንችለው
ሁሉ እስተዋጽዖ ማድረግ ይኖርብናል። ይህ እስተዋጽዖ የማበረታቻ የሀሳብ ድጋፍ ጀምሮ በሙያ እና በገንዘብ ድረስ የሚደርስ ድጋፍ
ሊሆን ይገባል።

በዚህ ሀገራዊ እና ህዝባዊ ጥረት ማንም ገለልተኛ መሆን ስለማይገባው ሁላችንም በምንችለው ሁሉ እንድንሳተፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት ድርጅት፣
ኢሳትን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃዎችን ወይም ቃለመጠየቅ በማድረግ ቢያንስ የአማካሪ ቦርድ ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ አበበ በለውን
በስልክ ቁጥር +12404724439 ወይም በኢሜል abelewd@yahoo.com ወይም
የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑትን አ ቶ ፋሲል የኔአለምን በ0031 455 112993 ወይም በኢሜል bikoetht@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።

www.ethsat.com