የአፋር ወጣቶች የጅቡቲን መስመር ዘግተው አመሹ

የአፋር ወጣቶች የጅቡቲን መስመር ዘግተው አመሹ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 08 ቀን 2010 ዓ/ም) ወጣቶቹ እርምጃውን የወሰዱት ከህዳር 26 ጀምሮ በደህንነት አባላት ታፍኖ ከተወሰደ በሁዋላ እስከዛሬ ድረስ ያለበት ያልታወቀው የሰመራ ዩኒቨርስቲ የሰው ሃይል አስተዳደር ሃላፊ አቶ ሳሊህ ረሺድ እንዲፈታ ለመጠየቅ ነው።
ወጣቶቹ በሌሊት የጅቡቲን መንገድ በመዝጋት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲስተጓጎል ያደረጉ ሲሆን፣ የክለልዩ ልዩ ሃይል ወደ ስፋረው በመጓዝ መንገዱን አስከፍቷል። ወጣቶች መንገዱን ከዘጉ በሁዋላ በመሰወራቸው ሳይያዙ ቀርተዋል።
የሰመራ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በግቢያቸው ውስጥ አቶ ሳሊህ እንዲፈታ የሚጠይቁ መፈክሮችን በብዛት ለጥፈው በማደራቸው፣ ዘይኑ ጆሃር፣ ከድር አሊና የሰመራ ዩኒቨርስቲ የጥበቃ ሃላፊ መታሰራቸውን የአካባቢው ተወላጆች ገልጸዋል።
ወጣቶች ወደ አብዴፓ ጽ/ቤት በመሄድ አቶ ሳሊህ እንዲፈታ የጠየቁ ቢሆንም እስካሁን መልስ አላገኙም።
አቶ ሳሊህ ባለፈው ህዳር ወር በአፋር የተከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አስታኮ የተያዙ ናቸው። የህወሃት የመከላከያ አዛዦች በክልሉ ውስጥ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወማቸው ወታደራዊ አዛዦቹ ሲዝቱባቸው እንደነበር ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ የአካባቢው ተዋላጆች ገልጸዋል።