የአርመንያው ፕሬዝዳንት ከስልጣን ለቀቁ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 15/2010) የአርመንያው ፕሬዝዳንት በሃገሪቱ የተቀሰቀሰባቸውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ተሰማ።

በቅርቡ ስልጣናቸውን ይለቃሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሰርዝ ሳርግስያን ባለፈው ማክሰኞ ራሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸውም ተሰምቷል።

ይህን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽም የሀገሪቱን ስልጣን አላግባብ ተቆጣጥረውታል የተባሉት ሰርዝ ሳርግስያን ስልጣናቸውን በግዴታ እንዲለቁ አድርጓቸዋል ተብሏል።

በአርመኒያ በተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኒኮል ፓሲኒያ የተጠራውን ተቃውሞ ተከትሎ የአርመኒያ ህዝብ አደባባይ በመውጣት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ስልጣናቸው እንዲለቁ ሲጠይቁ ከርመዋል።

ለተከታታይ ቀናትም ያደረጉትን ጠንካራ ተቃውሞ ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ሰርዝ ሳርግያንስ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል።

የሁለት ዙር ፕሬዝዳንታዊ ዘመናቸውን ጨርሰው ስልጣኑን ሊያስረክቡ ነው ተብሎ ሲጠበቅ  ጭራሹኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣኑን ባለፈው ማክሰኞ መያዛቸው ለተቃውሞው መቀስቀስ ምክንያት መሆኑንም ነው ቢቢሲ በዘገባው ያሰፈረው።

ፕሬዝዳንቱ በግል ድረገጻቸው እንዳሰፈሩት የህዝቤን ፍላጎት ለሟሟለት ስል ስልጣኑን ለቅቄያለሁ ብለዋል።

ከተቃዋሚው ከኒኮል ፓሺያን በተጨማሪ 2 ተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞውን መሳተፋቸውንና በቀናት ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ ሰልፎች ለእስር መዳረጋቸውን ነው ቢቢሲ የዘገበው።

አርመኒያን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ በፕሬዘዳንትነት ሲመሩ የቆዩት ሰርዝ ሳርግያንስ ሀገሪቱን ለከፋ ድህነት ጥለዋል ተብለው እንደሚወቀሱ ዘገባው አክሎ ገልጿል።

እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 የሃገሪቱ ህዝብ የመንግስትን ስልጣን ከፕሪዝዳንታዊ ወደ ፓርላማንተሪ ለማዞር ድምጽ መስጠቱና አሁንም ፕሬዝዳንቱ ግዜያቸውን ጨርሰው ይለቃሉ ሲባል ፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስተር እንዲሆኑ ድምጽ መስጠቱ የሕዝብን ተቃውሞ መቀስቀሱ ታውቋል።