የአለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር ተወሰነ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 20/2011) የ2019 የአለም የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ እንዲከበር መወሰኑን ዩኔስኮ በይፋ አስታወቀ።

የመገናኛ ብዙሃን ሚኒ በዲሞክራሲና ምርጫ ላይ በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከግንቦት 2 እስከ 3 በአዲስ አበባ የሚካሄደውን 26ኛውን የፕሬስ ነጻነት ቀን ዩኔስኮ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር ማዘጋጀቱ ታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ ትላንት በይፋ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ በአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት በሚካሄደው 26ኛው የፕሬስ ነጻነት ቀን ከመላው አለም ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ እንግዶች ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሰረት የፕሬስ ነጻነት ቀን በየአመቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 3 ቀን ይከበራል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1993 ጀምሮ ለ26 አመታት በቀጠለው አመታዊ ስነስርአት የፕሬስ ነጻነት እንዲከበር የመብት ተሟጋቾች ድምጻቸውን ሲስተጋቡ ቆይተዋል።

አመታዊው የፕሬስ ነጻነት ቀን መከበር ከጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1993 ጀምሮ ጋዜጠኞችን በወህኒ መጣል የዘወትር ተግባር አድርጋ በቆየችው ኢትዮጵያ ዛሬ አንድም ጋዜጠኛ አለመታሰሩ ወይንም እስር ቤት አለመኖሩ ታውቋል።

በዚህም አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች የሆነው ሲፒጂ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጠኞች ያልታሰሩባት ሃገር ሆናለች ብሏል።

በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ ከኢትዮጵያ መንግስትና ከአፍሪካ ሕበረት ጋር በመተባበር 26ኛውን የፕሬስ ነጻነት ቀን በኢትዮጵያ በሚያከብረው ዩኔስኮ የኮሚኒኬሽን ረዳት ዳይሬክተር በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ለዲሞክራሲያዊ ማሻሻያ በተለይም በሚዲያው ዘርፍና በሰባአዊ መብት ረገድ ያሳየውን ለውጥ አድንቀዋል።

26ኛው የፕሬስ ነጻነት ቀን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 3/2019 በኢትዮጵያ ደግሞ ሚያዚያ 25/2011 አዲስ አበባ ሲከበር የጉሌርሞ ካኖ የፕሬስ ነጻነት ሽልማት ስነስራአት ይካሄዳል።