የኖቤል አሸናፊዎች ታወቁ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 25/2011) የ2018 የሰላም ኖቤል አሸናፊዎች ታወቁ።

የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊወቹ  ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጄ የተባሉ ኮንጎአዊ እና ናዲያ ሙራድ የተባለች ኢራቃዊ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል።

ሁለቱም የሰላም ኖቤል አሸናፊዎች በግጭትና ጦርነት አካባቢዎች ወሲባዊ ጥቃት እንዲቆም በሰሯቸው ተግባራት መመረጣቸው ታውቋል።

የሰላም ኖቢል ሽልማቱን በጋራ ካሸነፉት መካከል የኮንጎ ዜግነት ያላቸው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጄ የማህፀን ሀኪም ናቸው። ዶክተር ዴኒስ ህክምና በመስጠትም ይታወቃሉ።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምስራቃዊ ግዛት ከነበረ ጦርነት ጋር በተያየዘ የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸውን ከ50 ሺህ በላይ ሴቶች አክመዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ኢራቃዊቷ ናዲያ ሙራድ ከአራት ዓመታት በፊት በእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ታግታ የወሲባዊ ጥቃት የደረሰባት ወጣት ስትሆን ይህንንም ለመታገል ከፍተኛ ትግል ስታደርግ ነበር ተብሏል።

ዘገባዎች እንዳመለከቱት 331 ይኖቢል ሽልማት ዕጩዎች  ቀርበው ነበር ።

ከእነዚህም መካከል 216 ታዋቂ ግለሰቦች ናቸው 115ቱ ደግሞ ቡድኖች ውይም ተቋማት መሆናቸው ነው የተነገረው።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ በኖቤል ሽልማት አሰራር መሰረት ዕጩዎች ለህዝብ ይፋ የሚደረጉት ከ50 ዓመት በኋላ ነው ።

በዘንድሮው የ 2018 የሰላም ኖቤል ሽልማት የሁለቱ ኮሪያ መሪዎች አሸናፊ ይሆናሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር።

ሁለቱ መሪዎች በሁለቱ ሃገራት መካከል የቆየውን ውጥረት ለማርገብ የወሰዷቸው እርምጃዎች የሽልማቱ ተመራጭ ያደርጋቸዋል የሚሉ በርካቶች ነበሩ።

ሌላው ሽልማቱን ሊያሸንፉ ይችላሉ ተብለው ቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው መሪዎች መካከል እንዱ ዶናልድ ትራምፕ ናቸው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሪያ ባህረሰላጤ ሰላም ለማስፈን እንዲሁም ሰሜን ኮሪያ ኒዩክለር ቦንብን ከማበልጸግ እንድትቆጠብ ለጀመሩት ጥረት ሽልማቱን ሊያገኙ ይችላሉ ተብሎም ነበር።

ይሕም ሆኖ ግን አምስት አባላት ያሉት  ኮሚቴ የዘንድሮወን የሰላም ኖቢል ሽልማት ለኮንጎአዊው ሀኪም ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጄ እና ለሰብአዊ መብት ተከራካሪዋ ኢራቃዊ ናዲያ ሙራድ መስጠቱን ይፋ አድርጓል።