የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ስጋትን የሚገልጽ የድምጽ ቅጂ ይፋ ሆነ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 8/2011) ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ችግር እንዳለባቸው በመግለጽ የተለያዩ የአሜሪካን አየር መንገዶች ውስጥ የሚሰሩ አብራሪዎች ስጋታቸውን የገለጹበት የድምጽ ቅጂ ይፋ ሆነ።

በሌላ በኩል የትራምፕ አስተዳደር የአቪዬሽን ባለስልጣናት ችግሩ የቦይንግ ሳይሆን የአብራሪዎቹ በቂ ስልጠና አለማግኘት ነው የሚል መከራከሪያ ይዘው መምጣታቸው ውዝግብን ፈጥሯል።

የቦይንግ ኩባንያን ስም ለመከላከል ጥፋትን መደበቅ አይገባም የሚል ተቃውሞ በአሜሪካን ፖለቲከኞች እየተነሳ ነው።

ጉዳዩ ሁለቱን የአሜሪካ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ፍጥጫ ውስጥ መክተቱን በኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ የደረሰን አደጋ ተከትሎ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ የገባው ቦይንግ ኩባንያ በአሜሪካውያን ፖለቲከኞች ዘንድ ፍጥጫን ባስተናገደ ጉዳይ ስሙ እየተነሳ ነው።

የአክሲዮን ዋጋው ላይ ጉዳት የደረሰበትና ትርፋማነቱ አደጋ ውስጥ የገባበትን የቦይንግ ኩባንያን ለመታደግ በሪፐብሊካን ፓለቲከኞች በኩል አዲስ ክርክር መነሳቱን ነው ኒውዮርክ ታይምስ የዘገበው።

ሰሞኑን የበርካታ የአሜሪካን አየር መንገዶች ውስጥ የሚሰሩ አውሮፕላን አብራሪዎች በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ከባድ የሆኑ ጉድለቶች እንዳሉት በመግለጽ ያቀረቡት አስተያየት በድምጽ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ እጅ መግባቱ ተመልክቷል።

በተቀረጸው ድምጽ ላይ ስጋታቸውን የሚገልጹት የአሜሪካን አውሮፕላን አብራሪዎች አስቸኳይ መፍትሄ እንዲፈለግ የሚያሳስቡበት እንደሆነም ታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመከስከሱ ሶስት ወራት በፊት ከቦይንግ ኩባንያ ሃላፊዎች ጋር ስብሰባ የተቀመጡት የአሜሪካን ፓይለቶች ማክስ 737 የሚታይበት ችግር በአስቸኳይ ካልተቀረፈ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀው እንደነበር የድምጽ መረጃው ያመለክታል።

ቦይንግ ኩባንያም የአውሮፕላን አብራሪዎቹን ስጋት ወደ ጎን በማድረግ የሶፍት ዌር ማስተካከያ እናደርግለታለን በሚል ማለፋቸውን ነው የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ የሚያመለክተው።

ያን ጊዜ የአሜሪካን አውሮፕላን አብራሪዎች ስጋት ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ መጋቢት ወር ላይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ለ157 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አደጋ አይከሰትም ነበር የሚል መከራከሪያ ተነስቷል።

ጉዳዩ የአሜሪካንን ፖለቲከኞች ማፋጠጡንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሪፐብሊካን የሚመሯት የአሜሪካን የአቬየሽንና የበረራ ደህንነት መስሪያ ቤቶች የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ የደረሱትን አደጋዎች ከስልጠና ጋር በማያያዝ ቦይንግን የመታደግ ዘመቻ መጀመራቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።

የሪፐብሊካን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ፓውል ሚቼል በትላንትናው ዕለት በሰጡት አስተያየት የቦይንግ አውሮፕላኖችን ጥፋት ሳይሆን የአብራሪዎቹን ስልጠና የተመለከተ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

ሌላው የሪፐብሊካን ተወካይ ሳም ግሬቭስም የአብራሪዎቹ ስልጠና በአደጋው ምርመራ ወቅት ችላ ተብሏል የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።

የሁለቱ ሪፐብሊካኖች አስተያየቶች የቦይንግ ኩባንያን ለመታደግ በትራምፕ አስተዳደርና በሪፐብሊካን ፓርቲ በኩል የተጀመረውን ዘመቻ የሚያመላክቱ ናቸው ተብሏል።

ዲሞክራቶችና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ቦይንግ ኩባንያን ለመታደግ ጥፋትን ማመን የመጀመሪያው ርምጃ ነው በሚል እየተከራከሩ ነው።

በመሆኑም የቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ ያሉትን ጉድለቶች በይፋ አምኖ በማስተካከል ኪሳራን ማስቀረት ይቻላል ብለዋል ዲሞክራቶች።