የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ወደ አፋር ሊያመሩ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2011)በአፋርና ኢሳዎች መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለማብረድ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የሚመሩት ቡድን ወደ አካባቢው ሊያመራ መሆኑ ተገለጸ።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት በአቶ ሙስጠፋ ዑመር የሚመራው ቡድን ላለፉት 5 ሳምንታት በአፋርና ኢሳ መካከል ያገረሸውን ግጭት በቦታው ተገኝቶ ለመፍታት በዝግጅት ላይ ነው።

በሶማሌ ክልል ሽንሌ ዞን አይሻ ከተማ የአፋር ልዩ ሃይል የወሰደውን ርምጃ በመቃውም ሰልፍ ተደርጓል።

በአፋር በኩል መንግስት ግጭቱን እንዲያስቆም ጫና የሚፈጥር የመንገድ መዝጋት ርምጃ መወሰዱ የሚታወስ ነው።

ሁለቱ ወገኖች በግጭቱ ዙሪያ እርስ በእርስ በመወነጃጀል ላይ ናቸው። ለቀናት ተዘግቶ የነበረው የጅቡቲ መስመር መከፈቱም ታውቋል።

ባለፉት ሶስት ሳምንታት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተከሰተው ግጭት እስካሁን ከ40 በላይ ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። በመቶዎች የሚቆጠሩትን ለአካል ጉዳት ዳርጓል። ሺዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።

ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው አንዳቸው ላይ ክስ ያቀርባሉ። ጠብ ጫሪው ማን እንደሆነ በሶስተኛ ወገን ማረጋገጭ የሚሰጥ በሌለበት ሁኔታ ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርስ በመወንጃጀል ላይ ናቸው።

አፋሮች ግጭቱ የጎረቤት ሀገር እጅ አለበት፣ በኢሳዎች ጀርባ መሳሪያ አስታጥቀው አፋሮች ላይ ጦርነት ከፍተዋል ሲሉ ይከሳሉ።

ኢሳዎችም በአፋር ልዩ ሃይል እየተገደልን ነው በማለት ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል።

የአፋር ወጣቶች ለሶስት ቀናት ከጅቡቲ አዲስ አበባ የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት መንግስት ግጭቱን እንዲያቆም የጠየቁ ሲሆን ኢሳዎች በተራቸው የባቡር መስመሩን በዛሬው ዕለት መዝጋታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በሽንሌ ዞን አይሻ ከተማ የሶማሌ ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ በአፋር ልዩ ሃይል እየተወሰደ ያለው ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል።

የአፋሮችና የኢሳዎች ግጭት በተጠናከረበት በዚህን ወቅት ነው የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ወደ አካባቢው ለመሄድ የተዘጋጁት።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት አቶ ሙስጠፋ ዑመር ሰሞኑን ወደ ግጭቱ ቀጠና ያመራሉ።

ለዘመናት የዘለቀው የሁለቱ ወገኖች ግጭት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሌላ ሶስተኛ ወገን እጅ ገብቶበት መባባሱ ያሰጋቸው ፕሬዝዳንቱ በአስቸኳይ መርገብ ስለሚችልበት ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይነጋገራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ከሶማሌ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የኢሳ ማህበረሰብ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሰላም እጦት የሰነበተ ችግር እንደሆነ የሚገልጹት ምንጮች ሁለቱ ወገኖች በሚጎራበቱባቸው ሶስት ቀበሌዎች ላይ የህወሃት አገዛዝ የሰጠው ብያኔ ችግሩን እንዳባባሰው ነው የሚነገረው።

ኢሳዎች እንደሚሉት ከአራት ዓመት በፊት በህወሃት አገዛዝ ወደ አፋር ክልል የተከለሉት ሶስቱ ቀበሌዎች ላይ በአፋር ልዩ ሃይል የሚወሰደው የሃይል ርምጃ ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጻሉ።

አፋሮች በበኩላቸው የጅቡቲ መንግስት ኢሳዎችን ይደግፋል፣ የውጭ ሃይል ፍላጎት ያለበት ግጭት ነው ሲሉ ይከሳሉ።

የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር ግጭቱ በሚበርድበት ሁኔታ ላይ ከአካባቢው የሁለቱም ወገኖች ተወካዮች ጋር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

በዛሬው ዕለት በተራቸው የባቡሩን መስመር የዘጉት የሶማሌ ክልል ተወላጆች በአይሻ ከተማ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ መንግስት በአስቸኳይ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል።

በአፋር ክልል መንግስት በኩል ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።