የሰገን ዞንን እንደገና ለማዋቀር የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ነዋሪዎች ነቀፋም ድጋፍም እየገለጹ ነው

የሰገን ዞንን እንደገና ለማዋቀር የተወሰነውን ውሳኔ ተከትሎ ነዋሪዎች ነቀፋም ድጋፍም እየገለጹ ነው
( ኢሳት ዜና ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ/ም ) የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን በ2003 ዓ/ም ኮንሶ፣ ደራሼ፣ አማሮ፣ ሰገን ከተማ/ጉማይዴ/፣ ቡርጂ እና አሌን በማጣመር ከተመሰረተ በሁዋላ አልፎ አልፎ የተቃውሞና የግጭት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል። በተለይ የኮንሶ ህዝብ በዚህ ዞን ስር ለመቀጠል ፈቃደኛ ባለመሆኑ፤ የተለያዩ ተከታታይ ተቃውሞዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ የዞን መዋቅር ሲጠይቅ የቆየው የኮንሶ ወረዳ፣ የዞን ጥያቄው በሀምሌ ወር 2010 ዓ/ም መልስ በማግኘቱ የሰገን ዞን እንደገና ይዋቀራል ተብሏል።
መንግስት አጥንቶ ባቀረው አማራጭ ኮንሶን ዞን በማድረግ፣ ሰገን ከተማን (ጉማይዴ) ደግሞ በዚህ ዞን ውስጥ በወረዳ ወይም ልዩ ወረዳ ሆኖ ማወቀር ፣ወይም ኮንሶን ዞን በማድረግ ሌሎቹ ወረዳዎች ሆነው እንዲዋቀሩ ነው እቅዱ።
የሰገንን ዞን መፍረስ የሚቃወሙት የካባቢው ነዋሪዎች፣ ዞኑን ማፍረስ መሰረታዊውን አገልግሎት የማግኘት ችግር አይቀርፈውም ይላሉ። ዞኑም ባለበት እንዲቀጥል ይመክራሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ኮንሶን ዞን ለማድረግ በተደረገው ትግል ከፍተኛ ዋጋ መክፈላቸውን የሚገልጹት የኮንሶ ተወላጆች ውሳኔውን በመደገፍ አስተያየት ሰጥተዋል። በጉዳዩ ዙሪያ የዞኑን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። መልሳቸውን እንዳገኘን ይዘን እንቀርባለን
ዘገባውን ለማጠናከር የረዳንን አኪያ ኢምፓየር ኢንተርቴይመንትን ምስጋናችንን እንገልጻለን።