የራያዎች አንገብጋቢ ጥያቄ የማንነት ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 29/2011) የራያዎች ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ የማንነት እንጂ የልማት አይደለም ሲል የራያ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አስታወቀ።

ኮሚቴው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካዔል ዛሬ በአላማጣ ከተማ  በጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የተናገሩትን ተከትሎ ለኢሳት በላከው መግለጫ እንደገለጸው ማንነቴን መልሱልኝ ያለን ህዝብ በልማት የተስፋ ቃላት ለማዘናጋት መሞከር ከንቱ ድካም ነው ብሏል።

ብዙ ከማውራት ብዙ መስራት በሚል መሪ ቃል በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት የልዑካን ቡድን በአላማጣ የጀመረው ስብሰባ ለሶስት ቀናት ይቆያል ተብሏል።

ራያዎች ያልተሳተፉበት የሕወሃት ደጋፊዎች መድረክ ሲል የራያ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ስብሰባውን አጣጥሎታል።

በራያ ውዝግቡ አልበረደም። የትግራይ ልዩ ሃይል በብዛት በመስፈር ህዝቡን በጉልበት መፈናፈኛ አሳጥቶታል የሚለው ክስ ከራያ መብት ተሟጋቾች በመቅረብ ላይ ነው።

ከአንድ ወር በላይ የዘለቀው የራያው ተቃውሞ ከ10 በላይ ሰዎች በትግራይ ልዩ ሃይል እርምጃ መገደላቸው የሚታወስ ነው።

ከ500 በላይ የራያ ወጣቶች፣ ባለሀሃብቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በትግራይ የተለያዩ እስር ቤቶች ተወስደው በስቃይ ላይ ይገኛሉ ብሏል የራያ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ።

ራያዎችን በመሳሪያ አፈሙዝ አንገት እያስደፉ መግዛት አብቅቷል በሚል የተጀመረው ዘመቻን በመሪነት የያዘው የራያ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በዶክተር ደብረጺዮን የሚመራው የትግርያ ክልል መንግስት የልዑካን ቡድን በአላማጣ እያደረገ ያለውን ስብሰባ በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።

ኮሚቴው ባለጉዳዮቹን ራያዎቹን በእስር ቤትና በአፈና ስር አድርገው የትግራይ ተወላጆች የተሰበሰቡበት የአላማጣው ስብሰባ ትርጉም የለውም ሲል አጣጥሎታል።

የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካዔልና ሌሎች አመራሮች አላማጣ ህዝብ እያወያዩ እንደሆነ የዘገበው ሬዲዮ ፋና የውይይቱ ትኩረት የልማት ጉዳይ እንደሆነ ገልጿል።

የስብሰባው  መሪ ቃልም ብዙ ከማውራት ብዙ መስራት እንደሆነ ተመልክቷል።

ህወሃት ደቡባዊ ዞን በሚል ባዋቀረውና ከ27 ዓመት በፊት በወሎ ክፍለሀገር ስር የነበረው የራያ አከባቢ ባለፉት ስድስት ወራት የማንነት ጥያቄ ባነሱ ራያዎች ተቃውሞ በውዝግብ ውስጥ መቆየቱን ተከትሎ ወደ አላማጣ ያቀኑት የህወሀት መሪዎች ችግሩ የልማት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረስ በልማት ጉዳይ ላይ ያተኮረ ውይይት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።

በስብሰባው ላይ በራያዎች ስም የተገኙት ታዳሚዎች የመሰረተ ልማት ጥያቄ እንጂ የማንነት ጥያቄ የለንም ማለታቸውም ተገልጿል።

የራያ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ለኢሳት እንደገለጸው ሰብሳቢዎቹም ተሰብሳቢዎቹም ህወሃቶች ናቸው፡፡ ስለራያዎች ለመወሰን የትግራይ ተወላጆች የተገኙበት መድረክ ነው በማለት አውግዞታል።

ኮሚቴው ጨምሮ እንዳስታወቀው ሰሞኑን ቤት ለቤት በመዘዋወር እኛ ትግሬ እንጂ አማራ አይደለንም የሚል ቅጽ እንዲሞሉ በራዮች ላይ ወከባ በመፈጸም ላይ ነው።

ዶክተር ደብረጺዮን የልማት ጥያቄ ልንመልስ ነው የመጣነው ቢሉ እንኳን 27 ዓመታት የት ከርመው ነው ዛሬ የመጡት ሲል ይጠይቃል የራያ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ።

የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለጊዜው አንገብጋቢ አይደለም የሚለው ኮሚቴው የማንነት ጥያቄን ለማዳፈን በባዶ ተስፋ የተሞላ የልማት ዲስኩር ይዘው አላማጣ ለገቡት ዶክተር ደብረጺዮን ምላሽ በመስጠት ‘ከንቱ ሙከራ’’ ነው ሲል ገልጿል።

ስብሰባው ለሶስት ቀናት ይቆያል ተብሏል።

በሌላ በኩል በራያ ህዝቡ ለሌላ ዙር ተቃውሞ መዘጋጀቱ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በሃያል ጥያቄውን ለመጨፍለቅ የወሰነው የትግራይ መስተዳድር ከጀመረው የጉልበት አማራጭ በቶሎ ካልተለመለሰ የከፋ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የራያ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ስጋቱን በመግለጽ አስጠንቅቋል።

የራያ የሀገር ሽማግሌዎች ጥያቄውን ይዘው አዲስ አበባ እንደሚገኙም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።