ወጣት ሰይፉ ዓለሙ በማእከላዊ እስር ቤት አካላዊና በማንነቱ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንደተፈጸሙበት ለፍርድ ቤት ተናገረ

ወጣት ሰይፉ ዓለሙ በማእከላዊ እስር ቤት አካላዊና በማንነቱ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች እንደተፈጸሙበት ለፍርድ ቤት ተናገረ
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 12 ቀን 2010 ዓ/ም) በሽብር ክስ የተከሰሰው ወጣት ሰይፉ ዓለሙ በማእከላዊ እስር ቤት ቆይታው ወቅት በምርመራ ሥም የተፈጸመበትን ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች አስመልክቶ ለ19ኛው ወንጀል ችሎት በአካል ቀርቦ አሰምቷል።
ተከሳሹ ወጣት ሰይፉ ዓለሙ በማዕከላዊ እስር ቤት ቆይታው የደረሱበትን በደሎች አስመልክቶ ለችሎቱ ሲናገር ”በድብደባ ምክንያት ከመኝታዬ ተነስቼ ለሽንት መውጣት አልችልም። ዘሬን እየጠቀሱ ሲሰድቡኝ እና ኢሰብአዊ ድርጊቶች ሲፈፅሙብኝ ነበር። ጉራጌ ስራ እንጂ ፖለቲካ አያውቅም እየተባልኩ በመርማሪዎች ተሰቃይቻለሁ።
በግዳጅ ከማላውቃቸው ሰዎች ጋር መሳሪያ አስይዘው በግዳጅ ፎቶ አስነስተውኛል። ሴት መርማሪዎች ምራቃቸውን እየተፉ በኤሌክትሪክ ገርፈውኛል። ጉራጌ ሌብነት እንጂ ፖለቲካን የት ያውቃል? እየተባልኩ ምራቅ ይተፋብኝም ነበር። ጥይት ገዝተሀል፣ የሎጅስቲክ አባል ነህ፣ የግንቦት ሰባት አመራር ነህ እየተባልኩ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶብኛል።” ሲል ለመሃል ዳኛው ለገሰ ኃ/መስቀል በዝርዝር አስረድቷል።
ሰይፉ ዓለሙ አክሎም ”ሰውነቴ ላይ የሚታዩት እነዚህ ጠባሳዎች ከእናቴ ማህፀን ስወለድ ያገኘኋቸው ሳይሆኑ በማዕከላዊ በደረሰብኝ ድብደባ ምክንያት ሰውነቴ ላይ የቀሩ ናቸው። ይሄ ሁሉ ድብደባ ደርሶብኝ ሰውነቴም መግሎብኝ ህክምና እንኳን እንዳላገኝ ተከልክያለሁ። መርማሪዎቹ እየሰከሩ እየመጡ ከፍተኛ ድብደባ አድርሰውብኛል። የኢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኞች በተገኙበት ቀረፃ እየተካሄደ ተደብድቤያለው።
ከዚህ በፊትም ማዕከላዊ ተይዘው የገቡ የጉራጌ ብሄር ተወላጆችም ተደብድበዋል፣ ተኮላሽተዎል። በዚህ ብሄር ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ሊቆም ይገባዋል።” በአካሉ ላይ የደረሰበትን ጉዳቶች ከዚህ በፊት ለችሎቱ ገልጦ ያሳየ ሲሆን አሁን ግን ለችሎቱ ለማሳየት ልብሶቹን ለማውለቅ ሲሞክር ”ከዚህ ቀደም አየተነዋል” በማለት ዳኞቹ ከልክለውታል።
ማዕከላዊ ማለት የሲዖል መናሃሪያ ያለው ወጣት ሰይፉ ዓለሙ የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ መለሰ ዓለም ከደብዳቢዎች መሃከል አንዱ እንደነበሩ ለችሎቱ አሳውቋል።
በችሎቱ ላይ የመከላከያ ምስክሮች ሆነው የቀረቡት አቶ ተስፋዬ አያሌው፣ አቶ ፋአድ ሙሀመድ ዩሱፍ፣ አቶ አብዱልፈታ ሁንዴ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ስነ ስርዓት ቁጥር 27(2) መሰረት ተከሳሹ የሰጠው ቃል በግዳጅ መሆኑን መስክረዋል። ተከሳሹ የደረሰበትን ድብደባና ስቃዮች በመጥቀስ ለችሎቱ አስረድተዋል።
ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህግን ምስክሮችና የተከሳሾችን የመከላከያ ምስክሮች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዚያ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ መስጠታቸውን የአምደ መረብ ጸሃፊው ሙጅብ አሚኖ ዘግቧል።