ከአርባ ምንጭ ከተማ በምህረት የተለቀቁት ወጣት ባንተወሰን አበበና ጓደኞቹ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ

ከአርባ ምንጭ ከተማ በምህረት የተለቀቁት ወጣት ባንተወሰን አበበና ጓደኞቹ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ/ም) ገዥው ህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካና የሕሊና እስረኞችን በምህረትና በይቅርታ አለመልቀቅ የገባውን ቃል ተከትሎ በነጻ የተለቀቁት የአርባ ምንጭ ወጣቶች ዳግም ለእስራት ተዳርገዋል።
ወጣት ባንተወሰን አበበን ጨምሮ አብረውት የነበሩት ሶስት ወጣቶች በባጃጅ ተጭነው ሲጓዙ በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል። እስካሁን 14 ቀናት ታስረው ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና ወጣት ባንተወሰን በተናጠል ተለይቶ በአሰቃቂ እስር ቤት ውስጥ መታሰሩ እንዳሳዘናቸው ቤተሰቦቹ አሳውቀዋል።
የአርባ ምንጭ ወጣቶችን በማነሳሳት በገዥው ፓርቲ ላይ አመጽ ያነሳሳሉ፣ ሕዝብን ይቀሰቅሳሉ የሚሉ ምክንያቶች ለወጣቶቹ መታሰር በኮማንድ ፖስቱ በምክንያትነት ቀርቦባቸዋል።
ለዓመታት ካለ ፍትሕ ታስረው ሰቆቃ ሲፈጸምባቸው ቆይቶ በነጻ የተለቀቁ ወታጣቶችን ድጋሜ እንዲታሰሩ ማድረግ አገዛዙ ለሕዝቡ የገባውን ቃል አጠያያቂ ያደርገዋል ሲሉ ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል።
በአርባ ምንጭና አካባቢው ያሉት የፖሊስ፣ የጸጥታና የመስተዳድር አካላት የህዝቡን የፍትሕና ዴሞክራሲ ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ አለመሆናቸው እንዳሳዘናቸው ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
በሌላ በኩል ከደሴ ከተማ የተያዙት ወጣት መኳንንት ካሳሁንና ጓደኞቹ በእስር ቤት ውስጥ ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።
ከደሴ ከተማ ተይዘው ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ በማእከላዊ እስርቤት በምርመራ ሥም ኢሰብዓዊ ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸው በሰማያዊ ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን የወጣቶች አደረጃጀት ኃላፊ ወጣት መኳንንት ካሳሁን አስታወቀ።
በማእከላዊ እስር ቤት ምርመራ ወቅት በቃል የማይነገሩ ሰቆቃዎች በምርመራ ላይ እንደደረሰበት ገልጿል። የመርማሪዎቹ ማንነት እንደማይታወቅ፣ ጥፍራቸው እንደሚነቀል፣ የሃሰት ምስክሮችን በማዘጋጀት ተወንጅለዋል። በየ28 ቀኑ ችሎት ቢቀርቡም በአራት ወራት ውስጥ የደረሰባቸውን የመብት ጥሰቶች ፍርድ ቤቱ ለይስሙላ የተሰመ በመሆኑ ሊታደጋቸው አለመቻሉን ወጣት ካሳሁን ገልጿል።
በእርስ ቤትና በምርመራ ወቅት በድብደባ ዘራቸውን እንዳይተኩ የተኮላሹ፣ በድብደባ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተው ማእከላዊ ውስጥ በሚስጥር የተቀበሩ፣ በግርፋት ሳቢያ የነርቭ ሕመም የታመሙና አያሌ ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው እስረኞች አሉ። ”የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሁን በኋላ ከትግሉ ወደኋላ ሳያፈገፍግ በጽናት መታገል አለበት። በጽናት ውስጣችን ጠንክረን የኢትዮጵያን እጣፈንታ እስከምናውቅ ድረስ እስከ መስዋእትነት ትግላችንን አናቆምም” ሲል ወጣት ካሳሁን መልእክቱን አስተላልፍዋል።