ኢፈርት ተጠሪነቱ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት እንዲሆን ተወሰነ

 (ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2011)ግዙፍ ፋብሪካዎችንና የንግድ ተቋማትን የሚያስተዳድረው የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅት (ኢፈርት) ተጠሪነቱ ለትግራይ ክልል ምክር ቤት እንዲሆን ተወሰነ።

ኢፈርት በሚል አህፅሮት የሚታወቀው በትግራይና የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚንቀሳቀሰው የሕወሃት ድርጅት ንብረት ተጠሪነቱ ወደ ትግራይ ክልል ምክር ቤት እንዲተላለፍ የተደረገው በህዝብ ተደጋጋሚ ጥያቄ መሰረት ነው ተብሏል።

ኢፈርትን በተመለከተ በተለይም  በድርጅቱ ተጠሪነት ጉዳይ እና የፋይናንስ ግልፅነት ላይ ጥያቄዎች ሲነሱ ቆይተዋል።

የሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ አመራሮች ኢፈርት በ17 አመታቱ የትጥቅ ትግል ዘመናት የተሳተፉ የቀድሞ ታጋዮች እና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ እና የትግራይ ክልልን መልሶ ለመገንባት የተቋቋመ የኢንዶውመንት ድርጅት ነው።

ይሕም ሆኖ ግን ኢፈርት በከፍተኛ ንግድ በመሰማራት የሀገሪቱን ሀብት በእጅ አዙር የዘረፈ ድርጅት እንደሆነም ሲነገር ቆይቷል።

በተለይም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ንግድ ባንክ ያለመያዣ ዋስትና በቢሊየን የሚቆጠር ብድር በመውሰድና ገንዘቡን ባለመመለስም ባንኮችን ለከፍተኛ ችግር የዳረገ መሆኑም ይታወቃል።

የተበላሸ ብድር እየተባለ ከብድር ነጻ ሲደረግ የቆየው ኢፈርት ከታክስ ነጻ በመሆኑም የሀገሪቱን ገንዘብ በእጅ አዙር የመዘበረ ተደርጎም ይወሰዳል።

በኢፈርት ሥር የሚገኙ ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ፤ በግብርናና እና በአገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ናቸው።

ከእነዚሁም ጉና ንግድ ድርጅት፣ መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፤ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ ሸባ ሌዘር ኢንዱስትሪ ይገኙበታል።

በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩት ትራንስ ኢትዮጵያ ፤ መስፍን ኢንጂነሪንግ፣ ሱር ኮንስትራክሽንን የመሳሰሉ ኩባንያዎችንም በስሩ አካቷል።

ኤፈርት  ተጠሪነቱ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲሆን ቢደርግም በአወቃቀሩ ለውጥ ስለመደረጉ የተገለጸ ነገረ አለመኖሩን የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውና በእነ አቶ በረከት ተመዝብሯል የሚባለው ጥረት የተሰኘው ድርጅትም ተጠሪነቱ  ከዚህ ቀደም ለአማራ ክልል ምክር ቤት መደረጉ ይታወሳል።