አባ ገዳዎች ወደ ወለጋ ሊሄዱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2011)የኦሮሞ አባ ገዳዎች ወደ ወለጋ ሊሄዱ መሆኑ ተገለጸ።

በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ የተከሰተውንና በርካታ ሰዎች ለተገደሉበት ግጭት መፍትሄ ለማፈላለግ አባገዳዎቹ በመጪው ሳምንት እንደሚንቀሳቀሱ ታውቋል።

ፋይል

ግጭቱ በሚካሄድባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ካሉ የህበረተሰብ ክፍሎች ጋር በመወያየት መፍትሄ ለማግኘት እንደሚጥሩም ተገልጿል።

በወለጋ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ የጸጥታ ስጋት ፈጥሯ ሲል መንግስት እየከሰሰ ነው።

ኦነግም ራሴን ለመከላከል ርምጃ ወስዳለሁ ብሏል።

ለወራት በዘለቀው የሰላም መደፍረስ ቀጠናው በቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከስድስት ወራት በላይ አካባቢው ሰላም አጥቶ ቆይቷል። አሁንም የተሻለ ነገር የለም።

ምዕራብና ምስራቅ ኦሮሚያ ለወራት በዘለቀው ግጭት ከሰው ህይወት እስከንብረት ውድመትና ዘረፋ የተፈጸመ መሆኑን መንግስት ሰሞኑን አስታውቋል።

የዞን ባለስልጣናትን ጨምሮ ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የገለጸው መንግስት ከ3ሚሊዮን ብር በላይ የባንክ ገንዘብ መዘረፉንም አስታውቋል።

በመንግስትና በኦነግ በካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ለስድስት ወራት አደባባይ ሳይወጣ የቆየ መሆኑን ያመነው መንግስት ጉዳዩን በትዕግስት ለማየት የሄድንበት ርቀት ዋጋ አስከፍሎናል ሲል ገልጿል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሰሞኑን እንዳስታወቀው ደግሞ የኦነግ ሰራዊት በሶስት አካባቢዎች ማሰልጠኛ ካምፖችን ከፍቶ እያሰለጠነ ነው።

የኦነግ ሰላማዊ ትግል ላይ ያለው አቋም አጠራጥሮኛል ነው ያለው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ።

ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ሲል ያስታወቀው ደግሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ነው።

ኦነግ በአቋሙ ጸንቶ ስምምነቱን ያፈረሰው መንግስት ነው የሚል ወቀሳውን በመያዝ ቀጥሏል።

ሁለቱ ወገኖች በዚህ ዓይነት ፍጥጫ ባሉበት ወቅት ነው አባገዳዎች ወደ ቀውሱ ቀጠና ለመጓዝ የተዘጋጁት።

የሬዲዮ ፋና ዘገባ እንደሚያመለክተው በምዕራብ ኦሮሚያ የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመፍታት የኦሮሞ አባ ገዳዎች በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ስፍራው ያቀናሉ።

አባገዳዎቹ የሰላምና የዲሞክራሲ ተምሳሌት ተደርጎ የሚታየው የአባ ገዳ ስርዓት በበቀለባት የኦሮሚያ ክልል ውስጥ አንድ ዓይነት ቀውስ መፈጠሩ ያሳዝናል ብለዋል።

ችግሩን በውይይትና በሰላም መፍታት እየተቻለ የአንድ እናት ልጆች መጋጨታቸው ተገቢ አይደለም ነው ያሉት አባገዳዎቹ።

የሃገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት መቻል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አባገዳዎቹ እንዳሉት በአካባቢው የሚኖረው ህዝብ ሰላም ፈላጊ በመሆኑ ክልሉን የግጭት አውድማ ከማድረግ ሁሉም አካል ሊቆጠብ ይገባል።

አለመግባባትን በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር ሊቆም እንደሚገባው አጽንኦት በመስጠትም ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸው ተገለጸ።

የፊንጫ የሃይል ማመንጫ ጠባቂዎች የሆኑትን ሁለቱን የፌደራል ፖሊሶች ማን እንደገደላቸው እንደማይታወቅ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።

ግድያው የተፈጸመው በትላንትናው ዕለት ነው።