አሜሪካ አልሸባብን ለመውጋት አዲስ እቅድ መንደፏ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 20 ፥ 2009)

አሜሪካ የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል አሸባብን ለመዋጋት አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫ መንደፏን የሃገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት አስታወቁ።

የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን ያዘጋጀው ይኸው የፖሊሲ አቅጣጫ የአሜሪካ ወታደሮች በቅርበት በታጣቂ ሃይሉ ላይ ጥቃትን እንዲፈጽሙ የሚጠቁም ሲሆን፣ አሜሪካ ለሶማሊያ መንግስት የምትሰጠው ወታደራዊ እገዛም እንዲጠናከር እቅድ መኖሩን ወታደራዊ ሃላፊዎቿ ለVOA እንግሊዝኛው ክፍል ገልጸዋል።

በኢራቅ በሶሪያ የሚካሄዱ ጥቃቶች ተጠናክረው በአዲስ መልክ እንዲቀጥሉ የሚጠይቀው የፔንታገን ረቂቅ ሃሳብ በሶማሊያው አልሸባብ ላይ ሁለገብ እና ተለዋጭ የሆኑ የአየር ጥቃቶች እንዲከናወኑም ይጠይቃል።

መኖሪያቸውን በአሜሪካ ያደረጉ የሶማሊያ ተወላጆች ወደ ሃገራቸው በመሄድ በአልሸባብ ሰልጥነው ወደ አሜሪካ ይገባሉ የሚል ስጋት ያላት አሜሪካ፣ ሃገሪቱ ልዩ ትኩረት የምትፈልግ እንደሆነም የአሜሪካ አፍሪካ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑ ጁኔራል ቶማስ ዊልድሃሰር ለአሶሼይትድ ፕሬስ ገልጸዋል።

አሜሪካ በሶማሊያ ጉዳይ አዲስ አቅጣጫን እና እይታን ትከተላለች ሲሉ የተናገሩት ጄኔራሉ ለዚሁ አዲስ ንድፍ የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ ሰራዊት ጋር አብረው እንዲሰማሩ እንደሚደረግም አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱ በሶማሊያ በጊዜያዊነት በዝውውር የምታሰማራቸው 50 ልዩ ወታደሮች ያሏት ሲሆን፣ ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችል እቅድ መኖሩን ለመረዳት ተችሏል።

አሜሪካ በሶማሊያ ለመከተል የያዘችውን አዲስ እቅድ የመከላከያ ሚንሲትሩ ጀምስ ማቲስ ያጸደቁት ሲሆን፣ ጉዳዩን ወደ ኋይት ሃውስ መምራታቸውን የዜና ወኪሉ በዘገባው አስፍሯል።

በሶማሊያ ተሰማርተው የሚገኙ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከሃገሪቱ ከሶስት አመት በኋላ ለቀው የመውጣት እቅድ እንዳላቸው በማሳወቃቸው ምክንያት አሜሪካ በታጣቂ ሃይሉ ላይ የምታካሄደውን ጥቃት በአዲስ መልኩ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ታውቋል።

አሜሪካ በሶማሊያ በተዘዋዋሪነት የምታሰማራቸው ወታደሮች በአሁኑ ወቅት ውስጥ የሆነ ጥቃትን የሚያከናውኑ ሲሆን በአዲሱ ሃሳብ ወታድሮቹ መጠነ ሰፊ ጥቃትን እንደሚያካሄዱ በሪፖርቱ መቅረቡን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ወታደራዊ መኮንኖች አክለው አስታውቀዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ሃገራቸው ከአዲሱ የአሜሪካዊ ዜግነት ካላቸው ፕሬዚደንት ሞሃመድ አብዱላሂ ጋር ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት መኖሩንም አክለው ገለጸዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር በሶማሊያ እየተካሄደ ያለውን ጸረ-አልሸባብ ዘመቻ ለማገዝ ከኢትዮጵያ ጋር ሲሰራ መቆየቱን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

ይኸው ትብብር ቀጣይ ይሁን አይሁን የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ የሚካሄደው የሽብር ዘመቻ አጠናክሮ ለመቀጠል ከግብፅ ጋር ተባብሮ ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።