በጅግጅጋ የበርካታ ሰዎች አስከሬን መውጣቱን ነዋሪዎች ተናገሩ

በጅግጅጋ የበርካታ ሰዎች አስከሬን መውጣቱን ነዋሪዎች ተናገሩ
( ኢሳት ዜና መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ/ም ) ባለፉት 2 ቀናት በጅግጅጋ ከቤተመንግስት ጀርባ ጋራው አካባቢ በርካታ አስከሬን መውጣቱን ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጻዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት በሁለት ቀናት ውስጥ የወጣው አስከሬን በመቶዎች ይቆጠራል። በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም ፡፡ ለክልሉ መንግስት ቅርበት ያላቸው ሰዎች አስከሬን መውጣቱን ቢያረጋገጡም ቁጥሩን እንዲሁም የቅርብ ይሁን የሩቅ አስከሬን የሚለውን ለማወቅ እንዳልቻሉ ገልጸውልናል።
ባለፉት 10 ዓመታት በክልሉ ውስጥ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ሰዎች ገልጸዋል። በክልሉ ከተፈጸመው ጅምላ ግድያ ጀርባ በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አብዲ መሃመድ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ወታደራዊ አዛዦች መኖራቸውን እነዚህ ወገኖች ይገልጻል።
የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በእስር ላይ ይገኛሉ። ከፍተኛ ገንዘብ እንዳላቸው የሚጠረጠሩ የእርሳቸው ደጋፊዎች፣ ፕሬዚዳንቱ እንዲፈቱ ተጽዕኖ ለመፍጠር የተቃውሞ ሰልፎችን ሳይቀር እያዘጋጁ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ።