በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ አምስት ተማሪዎች በቁጥጥር ስር

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2011)በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ከአንድ ተማሪ ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አምስት ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያ የህዝብ ግንኙነት ክፍል አስተባባሪ ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢሳት እንደገለጹት በግንቦት 16ቱ ግድያ የተጠረጠሩትና በድንጋይ ውርወራው እንዳሉበት የተደረሰባቸው አምስቱ ተማሪዎች ላይ ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ነው።

ተማሪውን ለግድያ ያበቃው ምክንያትንም በተመለከተ ምርመራ በመደረግ ላይ ነው ያሉት ኢንስፔክተር ጎበዜ፣ ግድያው በድንጋይና በስለት የተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች በተማሪው ግድያ ቁጣውን በመግለጽ መንግስት በአስቸኳይ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለፍርድ እንዲያቀርብ በመጠየቅ ዛሬ ስብሰባ አድርገዋል።