በደቡብ ጎንደር አንድ መስጊድ በእሳት ተቃጠለ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 4/2011)በደቡብ ጎንደር ትላንት ምሽት በአንድ መስጊድ ላይ የእሳት ቃጠሎ መድረሱ ተሰማ።

ፋይል

የእሳት አደጋው የደረሰው በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ጃራ ገዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሆኑንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

የዘር ግጭትን ወደ ሃይማኖት ግጭት ለመቀየር የሚጥሩ ወገኖች ይሄን ችግር እንደፈጠሩትም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

በቅርቡ በዚሁ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ከተማ ሁለት መስጊዶች መቃጠላቸውና በሶስተኛው መስጊድ ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱና ዝርፊያ መካሄዱን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በደቡብ ክልል ሃላባ ቂሊቶ ከተማ ሰባት የፕሮቴስታንት የሃይማኖት ስፍራ ላይ ጉዳት መደረሱ ተሰምቷል።

ጥቃቱ የተፈጸመውም በተደራጁ የከተማዋ ወጣቶች መሆኑንም መረጃው አመልክቷል።

በጥቃቱ የተጎዳ ሰው ስለመኖሩና ምን ያህል ንብረት መውደሙን ለማጣራት ኢሳት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።