በየመን ከሶስት ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች ከእስር እንዲለቀቁ አይ ኦ ኤም ጠየቀ

 (ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2011)በየመን በአስከፊ ሁኔታ በማጎሪያ እስር ቤቶች የሚገኙ ከሶስት ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች እንዲለቀቁ ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ጠየቀ።

ፋይል

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የገለጸው ድርጅቱ ኢሰብዓዊ በሆኑ የከፋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙትን እስረኞች ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተለያዩ የየመን አካባቢዎች የተያዙ እንደሆኑ አስታውቋል።

ከ2 ሺህ 500 ስደተኞች በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ስደተኞች በስታዲየም ውስጥ በስቃይ ላይ መሆናቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ።

ተላላፊ በሽታ በመዛመቱ የስደተኞቹ ህይወት አስጊ ደረጃ ላይ ይገኛል ብሏል አይ ኦ ኤም።

በአንድ እስር ቤት ውስጥ 14 ስደተኞች መሞታቸውንም ገልጿል።

የዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት መግለጫ እንደሚያሳየው አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ የሚነገርላቸው ከ3ሺህ በላይ ስደተኞች በከፋ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህም 2ሺህ አምስት መቶ የሚሆኑት ኤደን በተሰኘች የየመን ከተማ በሚገኝ ታዲየም ውስጥ በግርፋትና ድብደባ ስቃይ ላይ መሆናቸውን ነው ድርጅቱ ያስታውቀው።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደ አፈሳ በየእስር ቤቱ የታጎሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከኤደንና ላሂ በተሰኙ አካባቢዎች በስደት የገቡ ናቸው።

ጊዜያዊ ማቆያ በሚል የታሰሩባቸው ቦታዎች ለጤና አደገኛ የሆኑ ናቸው ተብሏል።

ከዚህ በተጨማሪ የየመን ታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ እንደሚፈጽሙባቸው ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

የአይ ኦ ኤም ሪፖርት ላይም ስደተኞቹ በጠባቂዎቻቸው ድብደባና እንገልት እንደሚፈጸምባቸው ተመልክቷል።

በስታዲየም በሚገኙት ኢትዮጵያን ስደተኞች ላይ ታጣቂዎች ተኩስ መክፈታቸውንና በርካታ ስደተኞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል፡፡

አይ ኦ ኤም እነዚህ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ነው የጠየቀው።

ተላላፊ በሽታዎች በመከሰታቸው በመጪዎቹ ጊዜያት የከፋ አደጋ እንደሚኖር አይ ኦ ኤም ስጋቱን ገልጿል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በአንድ እስር ቤት 14 ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው አልፏል።

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ስድተኞችን የመመለስ ስራ እያከናወነ እንደሆነም ገልጿል።

በላሂ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ 1400 ስደተኞች ታስረው እንደነበረ የገለጸው አይ ኦ ኤም በድርጅቱ ጥረት መለቀቃቸውን አስታውቋል።

ከእነዚህም 237ቱን ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መደረጋቸውንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጋ ተኮር በሆነው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካኝነት ጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ይላል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢሳት እንደገለጹት የየመኑ ጉዳይ በሂደት ላይ ነው በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያውያንን የመታደግ ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው ይላሉ።