በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ህገወጥ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2011)በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ዝርፊያን ጨምሮ የተለያዩ ህገወጥ ተግባራትን የሚያከናውነው ኦነግ ሳይሆን በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ናቸው ሲል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አስታወቀ።

በኦነግ ትዕዛዝ ስር የሚተዳደር ወታደራዊ ሃይል የለኝም ሲል ግንባሩ ገልጿል።

የኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ለመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዘጡት ቃለመጠይቅ እንደገለጹት ኦነግ ታጣቂ ሃይሎቹን ለአባገዳዎች አስረክቦ በሰላማዊ መንገድ ትግሉ ቀጥሏል።

በኦነግ ስም በዘረፋ ተግባር የተሰማሩት ቡድኖች ኦነግን አይወክሉም ብለዋል አቶ ቶሌራ።

መንግስት ጉዳዩን አጣርቶ እውነቱ ላይ መድረስ አለበት ሲሉ ጥሪ ያደረጉት አቶ ቶሌራ ኦነግ ባልሰራው እየተወነጀለ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃለአቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ኦነግ ወታደር የለውም ሲሉ የመጀመሪያቸው አይደለም።

በሰሜን ሸዋ አጣዬና በወሎ ከሚሴ ግጭት በተፈጠረበትና የኦነግ ስም በተጠቀሰበት ጥቃት ድርጅታቸው ምንም ዓይነት ሰራዊት የሚያዝ እንዳልሆነ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱ መግለጫ የሰጡት አንድ የኦነግ ሰራዊት ኮማንደር ነኝ ያሉ ግለሰብ የኦነግ ፖለቲካዊ አመራር የተለየ መሆኑን በመጥቀስ ወታደራዊ ክንፉ አሁንም ትግል ላይ መሆኑን ገልጸው ነበር።

ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይህንኑ አቋማቸውን በድጋሚ የገለጹት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ በአሁኑ ወቅት በኦነግ ትዕዛዝ የሚተዳደር ወታደራዊ ኃይል የለም ሲሉ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ግንባሩ ቀደም ሲል ታጣቂ ኃይል ነበረው ያሉት ቃል አቀባዩ ወታደሮቹን ለአባገዳ እና ለኦሮሞ ህዝብ ካስረከበ ወዲህ ወታደሮች የሉትም ሲሉ በቃለመጠይቃቸው ላይ ገልጸዋል።

ኦነግ የመነግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሀገር ቤት የገባው በድጋሚ መሳሪያ ለማንሳት አይደለም ሲሉ የገለጹት አቶ ቶሌራ ግንባሩ በአሁኑ ወቅት የትጥቅ ትግሉን ማቆሙን በይፋ ገልጾ መሳሪያ የሚያነሳበት ምንም ምክንያት አይኖርም ብለዋል።

በኦነግ ትዕዛዝ ስር የሚተዳደር ወታደራዊ ኃይል አሁን እንደሌለም አረጋግጣለሁ ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።

ምንም እንኳን ቃል አቀባዩ አቶ ቶሌራ ኦነግ ታጣቂዎች እንደሌሉት ቢገልጹም በተለያዩ አከባቢዎች በኦነግ ስም የሚካሄደው ጥቃት እንደቀጠለ ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በምዕራብ ጉጂ 10 ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት የኦነግ ስም ተጠቅሶ ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለ መነገሩ የሚታወስ ነው።

ኦነግ በሶስት አከባቢዎች አሁንም ይንቀሳቀሳል የሚለው የነዋሪው አስተያየት በኦነግ ስም የሚፈጸሙ ጥቃቶች አለመቆማቸው አሳሳቢ ደረጃ ይገኛልም ሲሉ አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ቶሌራ አደባ ግን በኦነግ ስም እየተንቀሳቀሱ የሚዘርፉ እንዳሉ አልሸሸጉም።

በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ቡድኖች አሉ ፣ቡድኖቹ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ እንጂ በድርጅት መልክ የሚንቀሳቀሱ አይደሉም ነው ያሉት አቶ ቶሌራ።

በዝርፊያ፣ በስርቆትና በመሰል ነገሮች የተሰማሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኦነግን መለያ ምልክት ይዘው መንገድ ላይ ተሽከርካሪ አስቁመው የሚዘርፉ እንዲሁም በኦነግ ስም በየመንደሩ እየተዘዋወሩ በሬ፣ ገንዘብ አምጡ የሚሉ ለዝርፊያ ብቻ ተሰባስበው የሚበተኑ ቡድኖች መኖራቸውን የጠቀሱተቶ ቶሌራ ይህን መንግስት አጣርቶ እውነቱን ማሳወቅ እንዳለበት በመግለጽ ጥሪ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅት ኦነግ የሚያደራጀው ሲቪልን ብቻ ነው አባሎቹም ሲቪሎች ናቸው ሲሉ አቶ ቶሌራ አደባ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።