በኦሮሚያ ክልል ከተሞች ትዕይንተ ህዝብ ተካሄደ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 25/2011)በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ግድያና መፈናቀል እንዲቆም የሚጠይቅ ትዕይንተ ህዝብ ተካሄደ።

ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በወለጋ፣ ምዕራብ ሸዋና ኢሉባቡር እየተደረጉ ያሉት ሰልፎች መንግስት አስቸኳይ የሆነ እርምጃ በመውሰድ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን አደጋ እንዲያስቆም የሚጠይቁ ናቸው።

በቅርቡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የምስራቅ ወለጋ አካባቢዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ፖሊሶችና ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞን እያሰማ ይገኛል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከኦነግ ያፈነገጠ ሃይል ጥቃት እየፈጸመ ነው ሲል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ ደግሞ ጥቅማቸው የቀረባቸው ሃይሎች ኦሮሚያ ክልልን ለመበጥበጥ ተነስተዋል ማለቱ ይታወሳል።

ሰላማዊ ሰልፎቹ የተካሄዱት በአምቦ፣ ጊምቢ፣ ሆለታ፣ ቡራዪ፣ ባኮ እና መቱን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ከተሞች ነው።

በሰላማዊ ሰልፎቹ ላይም በክልሉ በተለያዩ አዋሳኝ አካባቢዎች በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ እና ማፈናቀል  አውግዘዋል።

ይህንን ተግባር የፈፀሙ አካላት ለህግ ይቅረቡ የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችን ሰልፈኞቹ አሰምተዋል።

በዋናነት የተነሱት ጥያቄዎች ደግሞ በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግድያ እና ማፈናቀል ይቁም የሚሉ  ናቸው።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች ያለምንም ችግር መጠናቀቃቸውን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያጋጠመው የፀጥታ ችግር እንዲቆም የኦሮሚያ ክልል ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ጋር በጋራ እየሰሩ ናቸው።

ይሕም ሆኖ ግን  የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላት በተቀናጀ መንገድ በስልጠና እና በተለያየ ጦር መሳሪያ በመደገፍ በህዝቡ ላይ ጦርነት የከፈቱ በመሆናቸው ችግሩ በአጭር ሊቆም አልቻለም ተብሏል።

እናም በሁለቱ ክልሎች ስምምነት እና የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የፌደራል የፀጥታ አካላት ችግር ባጋጠማቸው አካባቢዎች በመግባት ርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

እስካሁን በተወሰደው ርምጃም ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው የተነገረው።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራ ገለጿል።

የክልሉ ካቢኔ ባካሄደው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመወያየት ውሳኔዎችን ማሳለፉን የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ቤጉህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ በክልሉ ለተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት የሆኑ አመራሮች ተለይተው ርምጃ እንዲወሰድባቸው መወሰኑን አስታውቋል።

በክልሉ ለተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሆኑ አመራሮች ተለይተው ተጠያቂ እንዲሆኑ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።

በቅርቡ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የምስራቅ ወለጋ አከባቢዎች በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ፖሊሶችና ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን ተከትሎ ህዝቡ ተቃውሞን እያሰማ ይገኛል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከኦነግ ያፈነገጠ ሃይል ጥቃት እየፈጸመ ነው ሲል የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/  ጥቅማቸው የቀረባቸው ሃይሎች ኦሮሚያ ክልልን ለመበጥበጥ ተነስተዋል ማለቱ ይታወሳል።