በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ስኬታማ እንዲሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ ሊታገዙ ይገባቸዋል። ወንጀል የፈጸሙ በህግ ይጠየቁ፣ ጉዳተኞች ካሳ እንዲያገኙና አፋኝ ሕጎች እንዲነሱ ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ገለጹ

በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ስኬታማ እንዲሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ ሊታገዙ ይገባቸዋል። ወንጀል የፈጸሙ በህግ ይጠየቁ፣ ጉዳተኞች ካሳ እንዲያገኙና አፋኝ ሕጎች እንዲነሱ ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ገለጹ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ/ም) በመላው ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት ህግን ተገን በማድረግ ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችና ተቋማት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ፤ ወንጀሎቹ በገለልተኛ አካል ተጣርተው ለህግ መጠየቅ አለባቸው። ጉዳተኞቹ ለደረሰባቸው ጉዳቶች ተገቢውን የሞራል ካሳ ሊያገኙ እንደሚገባና የሕግ ተቋማት ዳግም በባልሙያና በገለልተኛ አካል ሊዋቅቀሩ ይገባል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ።
የህግ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ እንዳሉት ‘’አፋኝ የሆነው የጸረ ሽብር ህጉና የወንጀለኛ አንቀጽ ህጎች መሻር አለባቸው። ይህን ያስፈጸሙ ግለሰቦች በህግ ሊጠየቁ ይገባል። በፌደራል ፖሊስ ውስጥ የጸረ ሽብር ግብረኃይል መፍረስ አለበት። ከህግ ውጪ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ህክምናን ጨምሮ የሞራል ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል። በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል የተፈጸሙት ወንጀልለኞች ጉዳይ በገለልተኛ ዓለም አቀፍ አካል ተጣርቶ በህግ መጠየቅ አለባቸው። በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ሊቆሙ ይገባቸዋል። አንድ ሽብርተኛ መንግስት ይቅርታ ጠይቆ አገር ሊያስተዳድር አይችልም። ስልጣኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማስረከብ አለባቸው።’’ ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴን በመጠቀም በውጭ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገራቸው መመለሳቸው መልካም ጅምር መሆኑን የህግ ባለሙያው አስምረውበታል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የራሳቸውን ሥርዓት መዘርጋት ይገባቸዋልም ብለዋል። ‘’አሁን ያለው አስተዳደር የሞግዚት አስተዳደር ሊያበቃ ይገባዋል። አገዛዙ ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዊያን ማስረከብ አለባቸው። ኢህአዴግ ማለት የቅኝ ግዛት ሥርዓት ማለት ነው። ህወሃት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመቆጣጠር የዘረጋው ስርዓት ማብቃት አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ገለልተኛ ተቋማትና መንግስት ሊያቋቁም ይገባል።’’ ሲሉ አቶ ተማም አባቡልጉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።
የሕግ ባለሙያ የሆኑት ጠበቃ አምሃ መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት ‘’ብዙ መስዋእትነት ተከፍሎ አሁን ላለንበት ለውጥ ደርሰናል። አሁን የተጀመረው የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ የለውጥ እንቅሳሴ መልካም ጅምር ነው። ጅምሩ ውጤታማ እንዲሆን በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ሊታገዙ ይገባቸዋል። ለውጡ ሊቀለበስ በማይችል ደረጃ ተጀምሯል። ከዚህ በኋላ ሁላችንም ዳር ቆመን መመልከትና ጉድለቶችን ብቻ እያጎላን ከመቀመጥ ቀረብ ብለን ለውጡን እየመራ ያለውን ኃይል ማገዝ አለብን። ብዙ የሚቀሩ ነገሮች አሉ። በተጀመረው ለውጥ ግን ደስተኛ ነኝ።’’ ብለዋል።
በመላው ኢትዮጵያ ለተፈጸሙ ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠበቃ አምሃ ሲመልሱ ‘’ዳግመኛ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች እንዳይደገሙ በማስረጃ ተደግፎ አጣሪ ኮሚሽን በገለልተኛነት ሥራውን እንዲሰራ መፍቀድ ያስፈልጋል። ተጨባጭ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች በህግ ሊጠየቁ ይገባል። ተቋማቱ በባለሙያ ሊመሩ ይገባል። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም አቤቱታ በቀላሉ የሚቀርቡባቸው ተቋማት ሊኖሩ ይገባል። ፍርድ ቤቶች ሚናቸው በጣም ወሳኝ ስለሆነ እንደገና ሊታዩ ይገባቸዋል። አሁን ባላቸው አደረጃጀት ይህንን ሚና ሊወጡ ይችላሉ ብዬ በኔ በኩል ብዙም እምነት የለኝም።” ሲሉ አቶ አምሃ መኮንን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።