በአደርቃይ የተከሰተው ግጭት መቀጠሉ ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 9/2010) በሰሜን ጎንደር ዞን አደርቃይ የተከሰተው ግጭት መቀጠሉ ተገለጸ።

ዛሬም

በማይጋባ ወንዝ አካባቢ በሚገኘው የወርቅ ማውጣት ስራ በተሰማሩ ሰዎች የተነሳው ግጭት በመከላከያ ሰራዊት የሚደገፉ የትግራይ ሚሊሺያዎች ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ አድማሱን በማስፋት መቀጠሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በግጭቱ ምክንያት በአደርቃይ ዛሬማና ሌሎች አነስተኛ መንደሮች የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ መቋረጡን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በቤንሻንጉል ጉምዝ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት እንደቀጠለ ነው።

በቀስት የተመቱ የአማራ ተወላጆች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል።

በሰሜን ጎንደር ዞን  አዲአርቃይ ዛሬማ ከተማና  በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች በመከላከያ የሚታገዙ የትግራይ ሚሊሺያዎች በህዝቡ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረውና በማይገባ ወንዝ ባለው የወርቅ ቁፋሮ ምክንያት እየተካሄደ ያለው ግጭት የትግራይ ሚሊሺያዎች መግባታቸውን ተከትሎ በመባባስ ላይ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምንም እንኳን ውጥረቱ ከጀመረ የቆየ ቢሆንም ወደ ግጭት ያመራው ሁለት ወጣቶች  በትግራይ ወርቅ አውጪዎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

በወቅቱ የአካባቢው የብአዴን አመራሮች ተጨማሪ አንድ የአማራ ተወላጅ መግደላቸው ህዝቡን በቁጣ ወደ ተቃውሞ እንዲወጣ አድርጎታል።

የብአዴን አመራሮች በስህተት የተገደለ ነው በሚል ሁኔታውን ለማረጋጋት ያደርጉት ጥረት አለመሳካቱን የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች የትግራይ ሚሊሺያ ወዲያውኑ ወደ አካባቢው በመድረስ ጥቃት መክፈቱን ነው ካደረሱን መረጃ ለማወቅ የተቻለው።

ግንቦት 3 ቀን በማይጋባ አካባቢ በወንዝ ዳር በባህላዊ የወርቅ ማውጫ ስፍራ ተጀመረ በተባለው ፀብ ሆን ተብሎ የህወሃት ሰዎች ወደ ብሄር የእርስ በርስ ግጭት እንዲያመራ አድርገውታል እየተባለም ነው።

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኘው የወርቅ ስፍራ የትግራይ ተወላጆች ወርቅ እያወጡ ይኖሩ እንደነበረ የአካባቢው ሰዎች ይገልጻሉ።

የአማራ ተወላጆች ከወርቁ ለመጠቀም በተንቀሳቀሱ ጊዜ ግጭቱ ሊፈጠር ችሏል ይላሉ ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች።

ግጭቱን ይበልጥ እንዲከር ያደረገው ደግሞ ለሽምግልና ከተላኩት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ መገደላቸው ሲሆን ግድያው  የህዝቡን ቁጣ ፈንቅሎት በሰላማዊ ሰልፍ  ወደ ዛሪማ ከተማ እንዲወጣ አድርጎታል።

የዛሬማ ከተማ አስተዳደር ለህዝቡ ቁጣ ምላሽ ሊሰጥ እንዳልቻለም ታውቋል።

አንዳንድ የብአዴን አመራሮች በግልጽ አቋም በመያዝ የአማራ ተወላጆች ለምን ወደ ወርቁ ስፍራ ሄዳችሁ በማለት እየተናገሩ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

በአሁኑ ጊዜ የትግራይ ሚሊሻዎች በዛሬማ ከተማ ገብተው ህዝቡን እያዋከቡት ነው። ተኩስ በመክፈትም ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል።

በግጭቱ የተገደሉት ወገኖችም በዋልድባ አባ ነፃ ደብር የቀብር ስነስርዓታቸው መፈጸሙ ታውቋል።

ህዝቡም የአፀፉ ርምጃ በመውሰድ በከተማዋ ያሉ ከአገዛዙ ጋር ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች ላይ ጥቃት መሰንዘሩንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በከተማዋ ባለው ከፍተኛ ውጥረት ምክንያት ተጨማሪ የህወሓት ወታደሮች እንዲሰፍሩ የተደረገ ሲሆን  ብዛት ያላቸው ወገኖች የተፈናቀሉና የተሰደዱ እንዳሉም ታውቋል።

ለተከታታይ ቀናት ከደበርቅ እስከ ሊማሊሞ መንገድ ዝግ ሲሆን የስልክ አገልግሎት ተቋርጧል።

በአደርቃይ ፣ዛሬማና በአካባቢው ባሉ መንደሮች የንግድ  እንቅስቃሴ ተገድቦ ያለ ሲሆን በአካባቢው አንዳንድ መንገዶች መዘጋታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።