በቡራዩ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት ከግለሰብ ጸብ ጋር የተገናኘ አይደለም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 8/2011) በቡራዩ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት በአንዲት የ6 ዓመት ሕጻን ላይ ከተፈጸመ አሰቃቂ ግድያ ጋር ተያይዞ ችግሩ ቢባባስም ጉዳዩ ከግለሰብ ጸብ ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳልነበር አቶ ለማ መገርሳ ገለጹ።

የብሔር ግጭት ለመፍጠር ታርጋ በሌላቸው ተሽከርካሪዎች አሰላ ድረስ የነበሩ የትንኮሳ ሙከራዎችም በሕዝብ ጥረት መክሸፋቸውን አስረድተዋል።

በቡራዩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማስመልከት ትናንት ሰኞ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት አቶ ለማ መገርሳ በዚህ አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት የተሳተፉ 200 ያህል ሰዎች መታሰራቸውንና የጦር መሳሪያዎችም መያዛቸውን ገልጸዋል።

ከፌደራል ፖሊስ ጋር በተቀናጀ መንገድ ምርመራ መቀጠሉን የገለጹት አቶ ለማ መገርሳ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

እስከ ትናንት ድረስ 300 ያህል አባወራዎች መመለሳቸውንም አስታውቀዋል።

ግጭቱ በአንዲት የ6 ዓመት ሕጻን ላይ በተፈጸመ አሰቃቂ ግድያ ቢባባስም የብሔረሰብና የሃይማኖት ጸብ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ይህንን ርምጃቸውን እስከ አሰላ ድረስ ለመውሰድ ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ያደረጉት ጉዞና ጥረት በህዝብ ጥረት መክሸፉን ገልጸዋል።

በተለይ በኦሮሞና በአማራ መካከል ግጭት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት መደረጉን የገለጹት አቶ ለማ መገርሳ የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር መመከሩንም አስታውቀዋል።

ይህች ሃገር የዛሬ 6 ወር ምን ያህል  ጨለማ ውስጥ እንደነበረች ሁላችንም እናስታውሳለን ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያን ከባህላዊ አስተዳደር ወደ ዘመናዊ አስተዳደር ለመውሰድ በሚደረገው ጉዞ እንቅፋት የሚፈጥሩ ወገኖችን አሳስበዋል።

እኩልነትና ፍትሐዊነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያን ለመመስረት ጥረት በሚደረግበት በአሁኑ ወቅት ሚዲያ ላይ ወጥተው ሕዝብን የሚለያይ ነገር የሚሰብኩ ወገኖችን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።

“ገፍተው ገፍተው ወዳልሆነ ነገር ሊከቱን ይፈልጋሉ” ያሉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ መቻቻል አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል አንድነትን ለመመስረት ለዘመናት ተለፍቶበታል፣ ለመለያየት ግን አንድ ቀን በቂ ነው ብለዋል።

የብሔረሰብና የዘር አጀንዳ ብሎም የነሱን የልዩነትና የጥላቻ ፖለቲካ የሚያራግቡትን ልናወግዝ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋነው ሕዝብን ለማቃቃር አይደለም ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ከጥላቻና የዘር ፖለቲካ ከማራገብ ተቆጥበን የሕዝብን አንድነትና ጉርብትናው ላይ ብንሰራ ጥሩ ነው ሲሉ መክረዋል።

አሁን በኢትዮጵያ መንግስት የተለወጠበት ሁኔታ ባይኖርም ከኋላቀር ወደ ዝመናዊ አስተዳደር በሽግግር ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ይህንን ወቅቱ ሁሉም በሃላፊነት ይንቀሳቀስ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።

“ሁሉ ነገር በማባበል ሊሰራ አይችልም” ያሉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ሐገሪቱ የወሮበሎች መፈንጫ እንዳይሆን ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

ቄሮዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ላመጣው ለውጥ የከፈሉትን ዋጋ ያስታወሱትና ያመሰገኑት አቶ ለማ መገርሳ ዛሬ በቄሮዎች ስም ዘረፋና ግጭት  የሚፈጥሩ መኖራቸውን በመግለጽ ቄሮዎችም እነዚህን አጋልጠው እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ቄሮዎች የታገሉት ለስርዓት አልበኝነትና ብሄረሰብን ለማጋለጥ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።