በቡራዩና አካባቢዋ 58 ሰዎች መገደላቸው ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 10/2011) በቡራዩና አካባቢዋ በተከሰተው ግጭት 58 ሰዎች መገደላቸውን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ።

አለም አቀፉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናልን በመጥቀስ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ከአርብ እስከ ሰኞ ባሉት ቀናት ውስጥ የ58 ሰዎች አስከሬን ታይቷል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪና ሪፖርት አጠናቃሪ አቶ ፍስሃ ተክሌ ከናይሮቢ ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል ለፈረንሳዩ  ዜና አገልግሎት ኤ ኤፍ ፒ በሰጡት መግለጫ ግድያው በዱላና በድንጋይ መፈጸሙን አመልክተዋል።

በደረሳቸው መረጃ መሰረት በጥይት የተገደለ አለመኖሩንም አመልክተዋል።

አርብ የ8 ሰዎች አስከሬን፣ቅዳሜና እሁድ ደግሞ የ21ና የ11 ሰዎች አስከሬን መገኘቱን መገኘቱን ተመራማሪው ነናግረዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ ሰኞ ዕለት ደግሞ ተጨማሪ 18 አስከሬን በአጠቃላይ 58 አስከሬን መገኘቱን የአይን እማኞችን በመጥቀስ ለፈረንሳዩ ዜና አገልግሎት ኤ ኤፍ ፒ ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኪሚስነሩ ዘይኑ ጀማል በቡራዩና አካባቢው የተገደሉ ዜጎችን ቁጥር በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ከ25 በላይ ሰዎች መገደላቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

የቡራዩ ከተማ የፖሊስ ሃላፊ ትላንት ለመንግስታዊው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ከግድያው ጋር በተያይዘ 364 ሰዎች መታሰራቸውን ገልጸዋል።

ከታሰሩት ውስጥ ከአዲስ አበባና ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ መኖራቸውንም አመልክተዋል።

የጦር መሳሪያዎችና የስለት መሳሪያዎች እንዲሁም ሶስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ በግጭቱ ወቅት ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጸጥታ አካላትና ሃላፊዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል።