በሶማሊያ የሚገኙ ሁለት ጎሳዎች አለመግባባታቸውን ለማስወገድ ተስማሙ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 10/2010) በሶማሊያ የሚገኙ ሁለት ጎሳዎች በመካከላቸው የቆየውን አለመግባባት ለማስወገድ መስማማታቸው ተሰማ።

ሳዳ ዮኒስና በኢዶ በተባሉት ጎሳዎች መካከል ለረጅም አመታት የቆየውን የእርስ በርስ ግጭት ለማስቆም  ሶስት ሳምንታትን የፈጀ ውይይት መደረጉም ታውቋል።

ሳዳ ዮኒስና በኢዶ በተባሉት ጎሳዎች መካከል ለረጅም አመታት በቆየው ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ሲዘገብ ቆይቷል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ የጎሳ መሪዎቹ ለሶስት ሳምንታት  ውይይት ማድረጋቸውንና በሰላም ለመኖር ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን አሳውቀዋል።

የሰላም ስምምነቱን በማያከብሩት ላይ ከበድ ያለ ቅጣት መወሰናቸውና ቅጣቱም የሞት ቅጣትን ጮምሮ አስከ 100 ሺ የሚደርስ የገንዘብ ክፍያን ያካትታል።

የሲያድባሬን መውደቅ ተከትሎ ላለፉት 27 አመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ሶማሊያ አንድ ብሄረሰብ ያለባት የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ሃገር መሆኗ ይታወቃል።

ሆኖም ላለፉት 27 ዓመታት በጎሳዎች ግጭት እና በእርስ በርስ ጦርነት እየተናጠች ትገኛለች።

ለግጭቶች መፈጠር እንደ መንስኤ የሚወሰዱት ለም መሬቶችንና የውሀ ቦታዎችን ለመውሰድ የሚደረጉ ሽሚያዎች መሆናቸውን ዘገባው አክሎ ገልጿል።

በዚህ አመት መጀመሪያ ብቻ ከ40 በላይ ሰዎች በአካባቢው በሚፈጠሩ ግጭቶች መሞታቸውን ዘገባው አስፍሯል።

በየወገኖቹ የሚደረገው የበቀል ርምጃ ደግሞ ለሰላም ሂደቱ አስቸጋሪ ሆኖ መቆየትን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።