በራሷ ችግር የተተበተበችው ኢትዮጵያ እኛን ለማደራደር ብቁ አይደለችም ስትል ደቡብ ሱዳን ገለጸች።

በራሷ ችግር የተተበተበችው ኢትዮጵያ እኛን ለማደራደር ብቁ አይደለችም ስትል ደቡብ ሱዳን ገለጸች።
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 12 ቀን 2010 ዓ/ም) ደቡብ ሱዳን ይህን ያለችው፣ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት በምህጻረ ቃሉ ኢጋድ፣ በደቡብ ሱዳን የእርስበርስ ግጭት ዙሪያ ለመምከር በሚቀጥለው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ስብሰባ እንደሚቀመጥ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ነው።
ኢትዮጵያ በራሷ የውስጥ ችግር እየታመሰች ባለችበት ሁኔታ፣ ለሯሷ መፍትሄ በመፈለግ ፋንታ ለደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች መፍትሔ ለመፈለግ የሚደረግን ስብሰባ ማዘጋጀት አትችልም ነው ያለው የሳልቫኪር መንግስት።
የደቡብ ሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትር ሚካኤል ሌውዝ መንግስታችን ለሰላም ድርድሩ የተያዘው ቀጠሮ ወደሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ይፈልጋል። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ችግር አለ በማለት ለራዲዮ ታማዙጅ መናገራቸውን ፣ የጁባው ኒያማይልፔዲያ ፕሬስ ዘግቧል።.
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አክለውም የሰላም ድርድሩ የሚደረግ ከሆነ በጅቡቲ፣በኬንያ አለያም በስ=ኡጋንዳ እንዲደረግ ሀሳብ አቅርበዋል። ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከጥያቄ ውጭ ናቸው ሲሉም አክለዋል።
ሁላችሁም እንደምታውቁት የወቅቱ ኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑት የኢትዮፕያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳይ እንኳ ገና መፍትሔ አላገኘም ሲሉም የደቡብ ሱዳኑ የማስታወቂያ ሚኒስትር ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በአስተዳደራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ባለመስማማታቸው ሳቢያ ባለፈው የካቲት በኢጋድ ተይዞ የነበረው የድርድር ፕሮግራም ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል።
በመሆኑም በዚህ ወር መጨረሻ ድርድሩ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ጁባ ኢትዮጵያ ለማደራደር ብቁ ስላልሆነች ድርድሩ የሚካሄድበት ሀገር እንዲቀዬው ያቀረበችው ጥያቄ የተያዘውን እቅድ ለሁለተኛ ጊዜ እንዳያጨናግፈው ተፈርቷል።
በሌላ በኩል ግብጽ በውስጥ ችግሯ ተጠርንፋ በተያዘችባቸው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዓባይ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጎን በመቆሟ ሳቢያ ካይሮ ጋር ተፋጥጠው የከረሙት የሱዳኑ መሪ ኦማር ሀሰን አልበሽር በበኩላቸው በአስገራሚ ሁኔታ በግብጽ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ከፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሢሲ ጋር በርካታ ስምምነቶችንና ውሎችን ተፈራርመዋል።
በየዕለቱ እንደ አየሩ ጠባይ በሚዋዥቀውና ለእርግጠኝነት ትንበያ በሚያስቸግረው የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ ከወራት በፊት ግብጽ በኤርትራ በኩል ጥቃት ልትፈጽምብኝ ነው በማለት የከሠሰችው ሱዳን ዛሬ ከካይሮ ጋር ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር ውል መፈራርሟ፣ በቀጣናው የኢትዮጵያ አቅምና ተፈላጊነት እየወደቀ መምጣቱን እንደሚያመላክት ተንታኞች ይገልጻሉ።
ኢጂፕት ቱዴይ እንደዘገበው አል ሲሲ እና-አልበሽር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 የተፈረመውን የአባይ ግድብ ስምምነት ለመተግበር እንዲሁም የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር፣የአባይ ወንዝ ሸልቆ አቅጣጫ ቅየሳ እና የድንበር ጉዳይ አስፈጻሚ ምክክር ኮሚቴ ለማቋቋምም ተፈራርመዋል።
ይህ የግብጽና የሱዳን አዲስ ቁርኝት በውስጣዊ አመጽ እየታመሰ ላለውና ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም፣ኡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ለመጣው የህወኃት አገዛዝ ከባድ ራስ ምታት እንደሚሆን ይጠበቃል።