በሞያሌ ግማሽ ቀን በፈጀ የተኩስ ለውውጥ በርካታ ሰዎች አለቁ

በሞያሌ ግማሽ ቀን በፈጀ የተኩስ ለውውጥ በርካታ ሰዎች አለቁ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ/ም) ትናንት እሁድ ከቀኑ 5 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት በነበረው የተኩስ ለውውጥ ከኦሮምያና ከሶማሊ በኩል በርካታ ዜጎች ተገድለዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ዛሬ ሞያሌ የሚገኙትን የኦሮምያ ፖሊሶች ትጥቅ አስፈትተዋቸዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ተሰደዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚገልጹት ትናንት ማንነቱን ያላወቁት አንድ እንግዳ ወደ ከተማዋ መግባቱን ተከትሎ ሶማሊዎች በሚኖሩበት አካባቢ የድንጋይ ውርወራ መጀመሩን፣ በኦሮምያ በኩልም የአጸፋ ተሰጥቷል። በድንጋይ ውርወራ የተጀመረው ግጭት ወደ 5 ሰዓት አካባቢ ወዲያውኑ ወደ መሳሪያ ተኩስ መለወጡን የሚገልጹት የአይን እማኞች፣ የኦሮምያ ፖሊሶችም ከሶማሊ ልዩ ሃይል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመከላከል ሲሉ የአጸፋ እርምጃ መውሰዳቸውን ገልጸዋል። ከባድ የጦር መሳሪያዎች ሳይቀር ይተኩሱ እንደነበር የሚናገሩት እማኞች፣ የሶማሊ ክልል ታጣቂዎች ለሳምንታት ምሽግ ቆፍረው በደንብ ሲዘጋጁበት እንደነበር ይናገራሉ።
በኦሮምያ በኩል የሚኖሩ ሰዎች እንደገለጹት እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ 7 ሰዎች ተገድለው የቀብር ስነስርዓታቸው ሲፈጸም፣ 37 ሰዎች ደግሞ ቆስለው ህክምና እየተደረገላቸው ነው።
በሶማሊ በኩልም የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ20 በላይ ሊሆን እንደሚችል ለኢሳት የደረሰው መረጃ ቢያመለክትም፣ ኢሳት በአካባቢው ከሚኖሩ የሶማሊ ተወላጆች ማረጋጋጥ አልቻለም።
በዛሬው እለት ህዝቡን ለመርዳት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች ትጥቃቸውን እንዲፈቱ መደረጉ የአካባቢውን ነዋሪዎች በእጅጉ አበሳጭቷል። የሶማሊ ክልል ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙ እየታዬ መከላከያ የሶማሊ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት ሲገባው የኦሮምያን ፖሊሶች ትጥቅ ማስፈታቱ ተገቢ አለመሆኑንና ይበልጥ ስጋት ውስጥ እንዲወድቁ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ግጭቱን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ወደተለያዩ አቅጣጫዎች መሰደዳቸውን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።