በሕንድ በአንድ ሆቴል በተነሳ ቃጠሎ 17 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2011)በሕንድ ደልሂ በአንድ ሆቴል ውስጥ ዛሬ ማለዳ በተነሳ ቃጠሎ 17 ሰዎች ሞቱ።

ቢቢሲ ከስፍራው እንደዘገበው በአብዛኛው ቱሪስቶች በሚበዙበትና ዋጋው ዝቅተኛ በሆነው አርፒት ፓላስ ሆቴል በተነሳው ቃጠሎ ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ የ17 ሰዎች ህይወት አልፏል።

ከሟቾቹ ከፊሉ እሳቱን ለመሸሽ በመስኮት ሲዘሉ መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን ብዙዎቹ የሞቱት ግን ታፍነው መሆኑን የአካባቢው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች የ35 ሰዎችን ህይወት የታደጉ ሲሆን የአደጋው መንሴ እስካሁን አልታወቀም።

አርፒት ፕላስ በተባለው በዚህ አደጋው በደረሰበት ሆቴል በወንድሙ ልጅ ሰርግ ላይ ለመታደም የተገኘው ሶምሻካር ለቢቢሲ እንደተናገረው በሰርጉ ለመታደም ከመጡት ቤተሰቦቹ የ84 ዓመት እናቱ እንዲሁም ወንድምና እህቱ በቃጥሎው ሞተዋል።