መሬታቸው ከጥቅም ውጭ የሆኑ አርሶ አደሮች ጩኸታችንን የሚሰማን አጣን አሉ

መሬታቸው ከጥቅም ውጭ የሆኑ አርሶ አደሮች ጩኸታችንን የሚሰማን አጣን አሉ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 03 ቀን 2010 ዓ/ም) በደቡብ ክልል፥ በጋሞ ጋፋ ዞን፥ የደምባ ጎፋ ወረዳ የጉራዴ ቀበሌ አርሶ አርሶ አደሮች ከኦቶሎ ሳውላ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ በመንገድ ሥራው ምክንያት በእርሻቸው ላይ ጎርፍ በመለቀቁ ማሳቸው በደለል፥ አሸዋና ጠጠር ተሞልቷል ::
እርሻችንን ማረስ አንችልም፥ ማሳችን ከጥቅም ውጭ ሆኗል የሚሉት አርሶ አደሮች፣ በተደጋጋሚ ለወረዳው አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርቡም ሰሚ ማጣታቸውን ፥ ለዞን አስተዳደር በደብዳቤና በአካል ቀርበው መጠየቃቸውን ፤ እንዲሁም ለደቡብ ክልል ቅሬታ ሰሚ አካል በደብዳቤና በአካል ቀርበው አቤት ብሉም ምንም መልስ ማጣታቸውን ተናግረዋል። “ላለፉት አምስት አመታት መፍትሔ ፍለጋ የተለያዩ በሮችን አንኳኩተናል፥ በትራንስፖርትና በአልጋ ኪሳችንን አራቁተናል፥ ድካምና እንግልት ደርሶብናል፥ ከአመራር አካላት ስድብና ዘለፋ ተፈራርቆብናል።ለረጅም ዓመታት ስናርስበት፥ ስንገለገልበት፥ ስንገብርበት፥ ልጆቻችንን ስናስተምርበት፥ ቤተሰቦቻችንን ስንመግብበት ለአገር ልማትና ዕድገት የደርሻችን ስንወጣ የኖርንበት መሬት ያለ ተገቢ ካሳና ተለዋጭ መሬት ሳይሰጠን መንገድ ተቀይሶበታል፣የጎርፍ መቀልበሻ ተቀዶበታል፤ከእርሻ ማሳችን ነፃ ወጥተን ከነቤተሰቦቻችን ሜዳ ላይ ወድቀናል። “ ብለዋል ።
ይኽ ሳያንስ የጉራዴ ቀበሌ ነዋሪዎች ሳይስማሙበት፥ ካለፊቃዳችን ከዚህ በፊት በደንባ ጎፋ ወረዳ ሥር ሲተዳደር የነበረን ቀበሌ ወደ ከተማ መዋቅር በራሳቸው ፈቃድ በማዛወር ለአትክልቶቻችንና በእርሻችን ላፈራነው እህል ተገቢ ካሳና ግምት ሳይከፍሉን መሬታችንን ለመቀማት የሚደረገው ዘመቻ ደም አፋሳሽ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል ።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በርብ የመስኖ ፕሮጀክት መሬታቸውን የተቀሙ 302 አርሶአደሮች እያንዳንዳቸው 22 ሺብ ካሳ ተከፈላቸው።አርሶ አደሮቹ የወደመባቸው ሃብትና ንብረት እንዲሁም ከጥቅም የሆነባቸው ማሳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ቢሆንም ፣ መንግስት ግን የገንዘብ ግሽበቱን ግምት ውስጥ ሳያስገባ እጅግ አነስተኛ ክፍያ መክፈሉ አርሶ አደሮች ገልጸዋል ::