130 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አርብ አስታወቀ

ኢሳት (ታህሳስ 21 ፥ 2009)

የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ 130 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አርብ አስታወቀ።

ለእስር ከተዳረጉት ሰዎች በተጨማሪ በስምንት ትላልቅ አክሲዮኖች በአራት ህንጻዎች በ49 ተሽከርካሪዎች፣ በ22 በመኖሪያ ቤቶችና በሁለት ፋብሪካዎች ላይ እገዳ መደረጉንም ኮሚሽኑን ዋቢ በማድረግ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰበር ዜና ዘግበዋል።

ይህንና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ለእስር የተዳረጉ የመንግስት ባለስልጣናትና ንብረት የታገደባቸውን ግለሰቦችና ተቋማት በስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

በ13 ተጠርጣሪዎች ላይ የሃብት ንብረት እገዳ መጣሉን የገለጸው ኮሚሽኑ ለእስር የተዳረጉት የመንግስት ባለስልጣናት ባለሙያዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ተመልክቷል። ከሁለት ቀን በፊት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተመሳሳይ መንገድ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 125 ግለሰቦችን ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።

በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ ነበሩ የተባሉት እነዚሁ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ላይ አስተዳደራዊ በደል ፈጽመዋል ሲል ኮሚሽኑ ይገልጻል።