ጫት በኢትዮጵያ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 25/2009)ጫት በኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ መድረሱንና የሀገሪቱን አምራች ዜጋ የከፋ አዘቅት ውስጥ እየከተተው መሆኑን በአንድ ጥናት ላይ ተገለጸ።
በማህበራዊ ጥናት መድረክ አማካኝነት የተደረገው ጥናት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የጫት አምባሳደር ሆነዋል ሲል አትቷል።
በአዳማ ናዝሬት ብቻ 3 ሺ የጫት ቤቶች እንዳሉ ተጠቁሟል።እንድ የዩኒቨርስቲ ተማሪ በጫት ስርቆት የተነሳ በተፈጠረ ጸብ ህይወቱ አልፏል ተብሏል።
ከሀገር ቤት የሚሰራጨው ሸገር ኤፍ ኤም ጥናት አቅራቢውን ዶክተር የራስወርቅ አድማሴን አነጋግሮ እንደዘገበው የጫት ጉዳይ የሀገሪቱ ብርቱ ፈተና ሆኖ ተደቅኗል።
ጥናቱ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ የተደረገ ሲሆን በውጤቱም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ እየሆነ እንደመጣ ያሳያል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሽዎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር የራስወርቅ አድማሴ ያቀረቡትን ጥናት በተመለከተ ሲናገሩ የዩኒቨርስቲዎችን መቋቋም እየተከተለ በከፈተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣው የጫት ንግድ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በበለጠ መልኩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችንና መምህራንን የሱስ ምርኮኛ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የአደጋውን ስፋት ለማሳየትም ጥናት አቅራቢው አንዳንድ አጋጣሚዎችን የጠቀሱ ሲሆን ተማሪዎች ለጫት ሱስ ቤተሰብ የሚልክላቸው ገንዘብ ስለማይበቃቸው ወደ ስርቆት ወንጀል የሚገቡ በርካቶች ናቸው ብለዋል።
ላፕቶፕ፣ሞባይልና የአልባሳት ስርቆት በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ እየተስፋፋ የመጣው ከዚሁ ከጫት ሱስ ጋር በተያያዘ እንደሆነም ተገልጿል።
ጥናት አቅራቢው አክለውም ከጫት እርሻ ውስጥ ጫት ለመስረቅ የገቡ 5 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የገጠማቸውን ያነሳሉ።
ተማሪዎቹ ከጫት ማሳ ውስጥ ገብተው በመስረቅ ላይ እንዳሉ ከጫቱ ማሳ ባለቤት ጋር በተፈጠረ ግብግብ አንደኛው ተማሪ ሕይወቱ ማለፉን ነው ዶ/ር የራስወርቅ የጠቀሱት።
የዩንቨርስቲ መምህራን ከጫት ሱስ ጋር በተያያዘ አደገኛ መስመር ላይ መሆናቸውን ያመለከተው ጥናቱ አደጋው ሀገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነም ጠቅሷል።
ዶ/ር የራስወርቅ እንደሚሉት በጫት ሱስ የተነሳ የመመረቂያ ወረቀት ከሚቀርብበት አዳራሽ ጥሎ የወጣው መምህር በጥናቱ እንደማሳያነት ተካቷል።
በተማሪዎች ማደሪያዎች ውስጥ ጫት መቃም የተለመደ ሆኗል። ያስከተለውም ቀውስ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
በሥልጣን ላይ ያለውና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ከጫት የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ በመሆኑ በጫት ንግድ ዝውውር ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር እንደማያደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአሜሪካ ነዋሪ የሆኑ ፕ/ር ህዝቅዬል ገቢሳ በጫት ዙሪያ ባደረጉት ጥናት ጫት የምግብን ቦታ እየተካ እንደሆነ ይናገራሉ።
ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ የእህል ማሳዎች በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ጫት እርሻነት ተቀይረዋል ሲሉም ይጠቅሳሉ። በኔዘርላንድ ሌይደን ዩንቨርስቲ የአፍሪካ ጥናቶች ማዕከል ተመራማሪ አቶ ገሠሠ ደሴ ባቀረቡት ጥናት ላይ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት ለጫት በጥቅም ላይ የዋለው መሬት 1.2 ሚሊየን ሄክታር ደርሷል።
ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ከ3 እጥፍ በላይ የሚሆን መሬት በጫት ተክል መሸፈኑን ነው አቶ ገሠሠ የገለጹት።
በጫት የሚገኘው ገቢ በጥፍ ጨምሮ ከመሰረታዊ የእህል ዓይነቶች ከሚገኘው የበለጠ በመሆኑ በሚሊየን የሚቆጠር ሄክታር መሬት በፍጥነት ሰፊ ጫት ማሳነት መቀየራቸውን የተለያዩ ጥናቶች አመልክተዋል።
የጫት ተክል የአየር ንብረት ለውጥ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለውም የሚያሳዩ ጥናቶችም ወጥተዋል።
በኢትዮጵያ እጅግ እየተስፋፋ ያለው የጫት ሱስ ማህበራዊ ህይወትን ባለፈው የመንግስት የሥራ ሰዓት በማስተጓጎል ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ መሆኑም ይነገራል።
ከቀትር በኋላ በርካታ የመንግስት ተቋማት ሠራተኞች በዚሁ የጫት ሱስ ምክንያት በስራ ገበታቸው የማይገኙ እንደሆነ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አደጋው ሰፊና ጥልቅ ነው የሚሉት ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ የገንዘብ ትርፍ ተገኘ ተብሎ ትውልድ እንዲጠፋ እየተደረገ በመሆኑ አፋጣኝ ሀገራዊ መፍትሄ ያሻል ብለዋል።
ይህ አስከፊ ሁኔታ አደገኛ ከሚባልበት ደረጃ ሁሉ አልፏል በጫት ምርትም ገበያ ላይ ጥብቅ መመሪያ ሊወጣ ይገባልም ብለዋል ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ።