ጥምረት ከሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች መካከል ሁለተኛው በሂውስተን ቴክሳስ ተካሄደ

የካቲት 20 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዚሁ ስብሰባ ላይ የግንቦት7 ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋለ፣ የኦነግ የስራ አስፈጻሚ አባልና የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ  የሆኑት አቶ አዴሳ ቦሩ እና ተዋቂው አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ በእንግድነት ተገኝተዋል።

የግንቦት 7 ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አበበ ቦጋል ጥምረት ለነጻነት፤ ለፍትሃና  ለእኩልነት በጄነራል ከማል ገልቹ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር ባለፈው ሳምንት ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ባደረገው የመጀመሪያው የጋራ ስብሰባ  አሁን አገራችን ከተዘፈቀችበት ችግር ለማውጣት ጥሩ ፖለቲከኛ መሆን ብቻውን በቂ አይደለም በማለት የተናገሩት የጥምረት ሊቀመንበር ንግግርን ጠቅሰው የአገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግር የተረዳ ሁሉንም በሆደሰፊነትና በአሪቆ አሳቢነት ማሰባሰብ የሚችል ባለራዕይ መሪ የሚያስፈልጉንን ያህል እንዲህ አይነት ባለ ራዕይ መሪ ለመፍጠር የሚችልና የገባንበትን ችግር በሚገባ ተረድቶ ከችግሩ ለመውጣት የሚደረገወን ትግል በሞራሉ ፤ በገንዘቡና በዕውቀቱ ለመርዳት ዝግጁ የሆነ ህብረተሰብም መኖር ወሳኝነት አለው ብለዋል።

በመቀጠልም በተለይ በትምህርቱ ፤ በገንዘቡና ነጻነት የሰፍነበት ህብረተሰብ ውስጥ ለመኖር ባገኘው ዕድል የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኘው የዲያስፖራ ኮሚኒቲ እንዲህ አይነቱን ህብረተሰብ ለመፍጠር ግንባር ቀደም ምሳሌና አረ አያ የመሆን ሃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበው ፤ በዘረኛው  አገዛዝ አገር እየፈረሰችን ዜጎች እየተፈናቀሉ ከዳር ቆሞ የሚመለከት ማንኛውም ሰው ታሪክ የፈጠረለትን አገር የማዳን ሃላፊነቱን ለመወጣት ዛሬውኑ ትግሉን ካልተቀላቀለ ከሂሊናና ከታሪክ ፍርድ አያመልጥም ሲሉ አሳስበዋል። በመጨረሻም ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ ከገባንበት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት የራሱን አስተዋጾ እንዲወጣ የትግል ጥሪ አቅርበዋል።

በጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ አዴሳ ቦሩ ግንባራቸው አሁን የወሰደው የፕሮግራም ለውጥ በወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመበት ያለውን የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ስቆቃ የሚፈጸምበትን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ካለበት ሲቃይ ሊገላግል የሚችል እርማጃ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ነጻ ሊወጣ የሚችለው ከኦሮሞ ጋር ተቀላቅሎ የሚኖረውና ከኦሮሞ ክልል ውጪ የለው አጠቃላይ ህዝባችን ነጻ ሲወጣ ብቻ ነው ያሉት የኦነግ አመራር አቶ አዴሳ ቦሩ፤ ድርጅታቸው አሁን የወሰደውን አቋም ለማጥላላት ሌሎች በተለይም ግንቦት 7 በፈጠረው ተጽእኖ  ነው ብለው የሚያስወሩ ሃይሎች የኦሮሞን ህዝብ ችግርና አገሪቱ በአጠቃላይ የገባችበትን ፈተና ለመረዳት ያልፈለጉ ናቸው ብለዋል።

ካረጀና ካፈጀ የፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥቶ አንድ እርምጃ መራመድ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ነው የሚሉት አቶ አዴሳ አዲሱ የኦነግ አቋም ሁሉንም ኢትዮጵያዊ አቅፎ የሚይዝ እንደሆነና ፍትህና እኩልነት የሰፈነበት ፤ በህዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሰረተች አዲስቷን ኢትዮጵያ መገንባት፣ የብሄር ብሄረሰቦችንና የግለሰቦችን መብት ማስከበር፣ ኦሮሚያ የአዲስቷ የፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ  ኢትዮጵያ አካል ማድረግ፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ከአማርኛ ቋንቋ ጋር እኩል የስራ ቋንቋ እንዲሆን ማድረግና የህግ የበላይነት በአገሪቱ እንዲሰፍን መታገል የሁላችንም የጋራ ሃላፊነት ነው ብለዋል።

ተዋቂው አርቲስት ታማኝ በየነ በበኩሉ የመለስ አገዛዝ በዘረኝነቱ ምክንያት ባለፉት 20 አመታት ከድጡ ወደ ማጡ እየተጓዘ መሆኑን አመልክቷል።

አርቲስ ታማኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻነት ካለ የተለያዩ ማህበረሰቦች አመለካካታቸውን፣ እምነታቸውን እና እራያቸውን ይዘው ተፈቃቅረው ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሪካዊ ማስረጃዎች እያጣቀሰ ገለጣ አድርጓል።

በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የስልጣን እርከኖች እና በውጭ አገር ባሉ ኢምባሲዎች ከፍተኛውን ቦታ የሚይዙት የህወሀት ካድሬዎች መሆናቸው አገሪቱ የገባችበትን ዝቅጠት ያሳያል ሲል አርቲስት ታማኝ አክሎ ገልጧል።

የተወካዮቹ ንግግር እንዳበቃ ከቤቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ተሰብሳቢውን እጅግ ያረካና ያስደሰተ ምላሽ በመስጠት ስብሰባ ው ተጠናቆአል።

በተመሳሳይ ዕለት በካሊፎርኒያ ግዛት በሳን ዮሴ አቶ ኤፍረም ማደቦ የጥምረት ስራ አስፈጻሚ አባልና አቶ አሚኑ ጂንዲ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዋና ጸሃፊ ተገኝተው ተመሳሳይ መግለጫ ሰጥተዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide