ገዚው ፓርቲ የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ላይ ያወጣውን መግለጫ ተቃወመ

ግንቦት ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአውሮፓ ፓርላማ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ.ር መረራ ጉዲና ከእስር እንዲፈቱና የቀረበባቸው ክስ ውድቅ እንዲሆን፣ በዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ ጃዋር ሙሃመድ ላይ የቀረበው ክስ እንዲነሳ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ከእስር እንዲፈቱ፣ በቅርቡ በኦሮምያና በሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጸሙ ግድያዎች የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚመራው ገለልተኛ ቡድን እንዲጣራ ያቀረበውን ጥያቄ፣ የኢህአዴግ አገዛዝ ተቃውሞታል። አገዛዙ የአውሮፓ ህብረት መግለጫ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ ያላስገባና በፍትህ ጉዳይ ጣልቃ እንደገባ የሚያስቆጥረው ነው ብሎአል።
ህብረቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፍጥነት እንዲነሳ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እንዲከበር ያወጣውን መግለጫ፣ ገዢው ፓርቲ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ አማካኝነት ተቃውሞውን አሰምቷል።
የአውሮፓ ህብረት ቀደም ብሎ ተመሳሳይ ውሳኔዎችን ቢያሳልፍም፣ ኢህአዴግ መራሹ አገዛዝ ለውሳኔዎች አወንታዊ መልስ ሲሰጥ አልታየም።