የፌዴራል ፖሊስ መርማሪዎች በፖለቲካ እሥረኞች ላይ የማሰቃያ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ምንጮቻችን አስታወቁ

ህዳር 28 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪዎች በፖለቲካ እሥረኞች ላይ የተለያዩ የማሰቃያ ወይም የቶርቸር ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ ምንጮቻችን አስታወቁ፡

ለታሳሪዎች ከቤተሰብ የሚመጣውን የዘወትር ምግብ ደግሞ በአብዛኛው የፌዴራል ፖሊስ አባላት ለእራሳቸው እንደሚመገቡት ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም ምርጫ ወዲህ በከተሞችና በክልሎች አካባቢ በሚነሱ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣  የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጥያቄዎች የደህንነት ሠራተኞችና የፌዴራል መንግሥት ፖሊሶች  በቁጥጥር ሥር የሚያውላቸው በርካታ ዜጎች ፣ ከክልል ከተሞችም ሆነ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እየተላኩ አሰቃቂ በሆኑ የማሰቃያ ዘዴዎች ምርመራ ይካሄድባቸዋል ፡፡

እንግልት፣ ሥድብ፣ ማንቋሸሽ፣ ድብደባ፣ ሆን ብሎ ማስራብና ማስጠማት፣ ግርፋት፣ ጨለማ ክፍል ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ለብቻ ማሰር፣ በቤተሰብና በሌሎች ሰዎች እንዳይጎበኝ ማድረግ፣ በውሃ የተሞላ በርሜል ውስጥ መንከር፣ ለሰዓታት የውሃ ጠብታ ግንባር ላይ እንዲንጠባጠብ ማድረግ፣ በኤልክትሪክ ንዝረት ማስጮህ፣ ሕመም ሲያጋጥም ለተወሰነ ጊዜ ሕክምና እንዳያገኝ ማድረግ፣ ሕክምና ሲቀርብም የሥርዓቱ ደጋፊዎች የሆኑ ሐኪሞች ጋር እንዲቀርብ በማድረግ በተዘዋዋሪ ፖሊሶች የሚጠይቁትን እንዲያምን መገፋፋት፣ በሌሎች እሥረኞች ላይ እንዲመሰክር ማግባባትና በጥቅማ ጥቅም ማሳመን እንዲሁም ቁልቁል ደፍቶ መቀመጫን መግረፍ፣ ብልትን መቀጥቀጥ የመሳሰሉት ድርጊቶች የዘወትር ተግባሮች ሆነዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎች በተለይም ወጣት የዩኒቨርስቲ፣ የመሰናዶ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ፣ ከትግራይ እና ከሌሎች ክልሎች በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ በእሥርና በሥቃይ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣  ከማዕከላዊ የሽብረተኝነት ክሥ ተመሥርቶባቸው ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስኪወሰዱ ድረስ አበሳቸውን እንደሚያዩና አንድ የማዕከላዊ እስረኛ ወደ ቃሊቲ ወረደ ከተባለ እንደ ደስታ እንደሚቆጠር አንድ የቢሮው ሠራተኛ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ የፌዴራል ፖሊስ ፣ ማዕከላዊን ጨምሮ ፣ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና ካምፖች የምግብ ማዘጋጃና የመመገቢያ ቦታዎች ያሏቸው ቢሆንም፣ በማዕከላዊ የመመገቢያ ቦታ የሚዘጋጀው ምግብ ከእሥረኞች ቤተሰቦች የሚገባውን የየቀኑ የምግብ ዓይነትና ብዛት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ምንጫችን ለዘጋቢያችን ገልጧል።

ረዕቡ፣ ዓርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ የሚመጣው የእሥረኛ ምግብ በተለምዶ በፖሊሶቹ ተለይተው ይታወቃሉ፣ ሲመገቡም በጋራና በሽሚያ ነው  ሲሉ አክለዋል፡፡

ቀደም ሲል ለተጠርጣሪ እሥረኞች ከቤተሰቦቻቸው የሚመጣው ምግብ የሚከለከለው እሥረኞቹ ተዳክመው ለመርማሪዎቻቸው ተባባሪ እንዲሆኑ እና በሚቀርብላቸው ደያስ እየተባለ በሚጠራ ምግብ የጤና ሥጋት እንዲያድርባቸው በሚል ነበር ያሉን የማዕከላዊ ሠራተኛ፣  ከቤተሰቦቻቸው የሚመጣው ምግብ በቆይታ እየተበላሸና ለየኔ ቢጢ እና ለጎዳና ተዳዳሪዎች እየወጣ ሲሰጥ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን እሥረኞቹ እየተበራከቱ በመምጣታቸው የምግቡ ብዛትም በመጨመሩ ለፌዴራል ፖሊሶች ተጨማሪ ምግብ ሆኖ ማገልገል ጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እሥር ቤት በፖለቲካና ሰብዓዊ መብት መከበር ጥያቄ መንሥዔ ብቻ ከሦስት መቶ ሰባ በላይ እሥረኞች አሉ ሲሉ የተናገሩት ሰራተኛው፣  የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት ሰባት አባልነት ተጠርጥረው የተያዙ ወጣት ተማሪዎች፣ የሃይማኖት ሰዎችና ነጋዴዎች ሲኖሩ ይህ ቁጥር በማዕከላዊ ቢሮ በደረቅ ወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎችን አያካትትም።