የፌደራል ፖሊስ አባላት ስራቸውን በገፍ መልቀቅ ያሳሰበው መንግስት ጥለው የሚጠፉ ፖሊሶችን ማሰር ጀመረ

ጥር 20 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከታማኝ የፌደራል ፖሊስ ምንጮች ባገኘነው መረጃ በመላ አገሪቱ የሚገኙ በርካታ የፌደራል ፖሊስ አባላት ስራቸውን እየለቀቁ ነው።

ባለፈው ወር ብቻ ከ100 በላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት ስራ መልቀቃቸው ያስደነገጠው መንግስት፣ ያለፈቃድ ጥለው የሚጠፉትን እያደነ በማሰር ላይ ነው።

ምንም እንኳ በትክክል የታሰሩ ፖሊሶችን ቁጥር ማግኘት ባይቻልም፣ በእየ ክፍለሀገሩና በማእከላዊ ወንጀል ምርመራ ውስጥ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ታስረው እንደሚገኙ ምንጮቹ አረጋግጠዋል።

ፖሊሶቹ ስራ የሚለቁበት ምክንያት የስራ ጫና ከሚከፈላቸው ደሞዝ ጋር አለመመጣጠኑ፣ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለው የአስተዳደርና የዘር መድሎ ነው።

በርካታ ፖሊሶች በቀን ውስጥ ከ16 ሰአታት ያላነሰ ስራ እንዲሰሩ እየተደረገ ቢሆንም፣ የሚከፈላቸው ደሞዝ ግን ከ800 ብር አይበልጥም ይላሉ የፖሊስ ምንጮች።

በርካታ ፖሊሶች የስራው ሰአት ይቀነስልን ወይም ደሞዝ ይጨመርልን ብለው ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ አማራ የሆነው ግንቦት7፣ ኦሮሞው ደግሞ ኦነግ እየተባለ እየተፈረጀ ይታሰራል።

እነ ጄኔራል ተፈራ ማሞ መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂዱ ነበር ተብሎ ከታወጀበት ከአመት በፊት እንዲሁም የኤርትራ መንግስት አዲስ አበባን ባግዳድ ለማድረግ አቅዶ ነበር የሚል ዜና በቴሌቪዥን ከተነገበት ጊዜ ጀምሮ፣ ጥበቃው በከፍተኛ ደረጃ በመጠናከሩ ፖሊሶች ስራው ከሀቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው በመግለጥ ስራውን ጥለው ይጠፋሉ።

በአረብ አገራት ከተነሳው አብዮት እንዲሁም በቅርቡ አኬላ ደማ የሚል ድራማ ከቀረበ በሁዋላ ደግሞ ፖሊሶቹ ያለእረፍት ከ16 ሰአታት በላይ እንዲሰሩ እየተገደዱ ነው። በየክልሎች የሚታዩቱ የጎሳ፣ የብሄር፣ የሀይማኖት እና የፖለቲካ ግጭቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚካሄዱት አለማቀፍ እና የአፍሪካ ህብረት ጉባኤዎች በፖሊሶች ስራ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው።

ፖሊሶች ጉባኤዎቹ በሰላም ከተጠናቀቁ በሁዋላ ምንም የሚከፈላቸው ገንዘብ ባለመኖሩ ወይም እረፍት እንዳይወጡ ስለሚደረጉ ለመጥፋታቸው ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።

በሌላ በኩል በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የሚታየው ዘረኝነት በርካታ ፖሊሶች ስራቸውን ጥለው እንዲጠፉ እያደረጋቸው ነው።

ብዙ ፖሊሶች በግል እና በመንግስት ኮሌጆች በራሳቸው ወጮ የማታ ትምህርት ተምረው  ዲፕሎማና ዲግሪ ቢይዙም፣ በመስሪያ ቤታቸው ውስጥ እድገት ለማግኘት አይችሉም። አብዛኞቹ ከፍተኛ ቦታዎች ስምንተኛ ክፍልን ባልጨረሱ የህወሀት ነባር ታጋዮች የተያዙ በመሆናቸውና ነባር ታጋዮቹም ዲፕሎማ የያዙትን ፖሊሶች እንደጠላት ስለሚቆጥራቸው፣ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ይጠፋሉ።

በፌደራል ፖሊስ ውስጥ በአማራ እና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያለው አድልኦም ሊገለጽ የሚችል አይደለም ይላሉ ታማኝ የፖሊስ ምንጮቹ ። በፌደራል ፖሊስ መስሪያ ቤት አንደኛ ፣  ሁለተኛ እና ሶስተኛ የሚባሉ የዜግነት አይነቶች አለ ይላሉ። የአንደኛ ዜግነት አባላት ነባር የህወሀት ካድሬዎች ሲሆኑ ሁለተኛ የዜግነት አባላት ደግሞ የኢህአዴግ አባላት ናቸው። ሶስተኛ ዜጎች የሚባሉት ተራ ፖሊሶች ሲሆኑ ፣ ባለማእረግ የኢህአዴግ አባላት ፖሊሶችም ሆኑ ተራ ፖሊሶች ለህወሀት ካድሬ ፖሊሶች መስገድ ግድ ነው ይላሉ።

የህወሀት ፖሊሶች ማንኛውንም አማራ ወይም ኦሮሞ ፖሊስ በጥርጣሬ አይን የሚያዩ በመሆኑ እርስ በርስ እየተጠባበቁ መኖር ግድ ሆኗል ሲሉ አክለዋል።

አንድ ፖሊስ 7 አመት አገልግሎት ከሰጠ በሰላም መሰናበት እንደሚችል ህጉ ቢደነግግም፣ ህጉ ግን ተግባራዊ እንደማይሆን ፖሊሶች ይናገራሉ።