የግንቦት7 7ኛ አመት ታስቦ ዋለ

ግንቦት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ግንቦት 7 ፣ 1997 ዓም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ልየ  ስፍራ የሚይዝ ቀን ነው። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ሁኔታ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዷል። ምንም እንኳ የመጨረሻ ውጤቱ ፣ እንደሂደቱ ያማራ ባይሆንም፣ ግንቦት7 አሁንም ዲሞክራሲያዊ ስርእት ተገንበቶ ማየት በሚሹ በብዙ ኢትዮጵያውያን አእምሮ ውስጥ እንደ አዲስ በእየአመቱ ይታወሳል።

ቀኑን በማስመልከት ግንቦት 7ትን ለ7ኛ ጊዜ ስንዘክር በሚል ርእስ ግንቦት7 ባወጣው ርእሰ አንቀጽ ” በግንቦት 7 1997 ምርጫ ሰበብ ሺህዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተለያዩ የአካል ጉዳቶች እንደደረሱባቸው፣  ከዚህ ቁጥሩ እጅግ በላይ የሆነ ሕዝብ ምናልባትም በሚሊዮኖች በሚቆጠር ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ለሆነ የሥነልቦና ጉዳት እንደተዳረገ እና የምርጫ 97ን ሕዝባዊ ድል ለማስጠበቅ ባለመቻላችን ምክንያት እና ይህንኑ የአቅም ማነስ ተከትለው በመጡ ተጨማሪ ችግሮች ሳቢያ የሚሊዮኖች ኢትዮጵያዊያን ቅስም መሰበሩን” አትቷል።

ግንቦት 7 ፣ 1997ን የምናስታውሰው በአንድ በኩል ነፃነት ካገኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎቹን መምረጥ የሚችል መሆኑ ያረጋገጠበት እለት በመሆኑ ግንቦት 7 ቀን 1997ን የምናስታውሰው በሃሴት ነው የሚለው ንቅናቄው፣  በሌላ በኩል ደግሞ ግንቦት 7  1997 ዲሞክራሲ ማለት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ ማለት አለመሆኑ በተግባር የተረዳንበት እለት ነው ብሎአል።

ንቅናቄው በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ያከናወናቸው ተግባራት በቂ ባይሆኑም ቀላል ግምት የሚሰጣቸው አለመሆናቸውን ጠቅሶ፣ በአራት ዓመታት እድሜው ውስጥ ያከናወናቸውን ስራዎች ሲጠቅስ፡ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ “ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ፀጥ አስደርጌዓለሁ” ባለበት ሰዓት “እንቢ! ለዘረኛ” ያሉ ወገኖች የተሰባሰቡበት በአገር ቤትና በውጭ አገራት ሰፊ መሠረት ያለው ድርጅት ለመሆን መቻሉን፤ የመለስ ዜናዊን የሚዲያ አፈናን በመገዳደር ኢትዮጵያዊያን ነፃ እና ሃቀኛ መረጃ የሚያገኙበትን መንገዶች በማፈላለግ ረገድ ብርቱ ጥረት ማድረጉን፣ በኢትዮጵያዊያን መካከል አድማሱን ያሰፋ ኅብረት እንዲኖር ጥረት ማድረጉንና ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች መታየታቸውን፣  ብዙዎች ለዓላማው መሳካት ሕይወታቸውን ሊሰውለት የሚፈቅዱለት፤ የመለስ ዜናዊን አገዛዝ እረፍት የነሳ፤ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን ተስፋ የፈነጠቀ ድርጅት ለመሆን መብቃቱን፣ በራሱ በመለስ ዜናዊ ወታደራዊ፣ አስተዳደራዊ እና የስለላ መዋቅር ውስጥ በመግባት የመለስ አገዛዝ እንዳይረጋጋ ለማድረግ መቻሉን አትቷል።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ባለመወገዱ ትግሉን እንደሚቀጥል ያስታወሰው ንቅናቄው ፣ ከባርነት ለመውጣት በጽናት መታገል ግድ እንደሚል አስምሮበታል።

የመለስ መንግስት ግንቦት7 ፣ 1997 ዓም የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ በንጹሀን ዜጎች ላይ በወሰደው እርምጃ ከ 200 በላይ መገደላቸው፣ ከ1000 ያላነሱ መቁሰላቸውና ከ30 ሺ ያላነሱ ታስረው መለቀቃቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide