የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሪ አያያዛቸውን የሚያሳይ መረጃ እንዲያቀርቡ ታዘዙ

ኢሳት (መጋቢት 18 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ በሃገሪቱ ያሉ ሁሉም የግል ባንኮች ካለፈው አመት ሃምሌ ወር ጀምሮ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጣቸውን የሚያሳይ መረጃ እንዲያቀርቡ አዘዘ።

ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባንኮች የሚያደርጉትን የውጭ ምንዛሪ አሰጣት እና አያያዝ በተመለከተ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አዲስ መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።

ይህንኑ መመሪያ በማድረግ ብሄራዊ ባንክ ሁሉም የግል ባንኮች ከሃምሌ ወር ጀምሮ ያካሄዱትን የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የአምስት ቀን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ባንኮቹም እስከባለፈው አርብ ድረስ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

በብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ክፍል ለባንኮቹ ተላልፎ በነበረው ደብዳቤ እያንዳንዱ ባንክ ውጭ ምንዛሪ የሰጡትን  አካልና መጠን በዝርዝር እንዲያስረዱ መጠየቃቸው ታውቋል።

በአይነቱ የመጀመሪያው እንደሆነና ባለፈው አመት ተግባራዊ በተደረገው መመሪያ መሰረት ሁሉም ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ የቀረበላቸውን ጥያቄ እንዲሁም ያስተናገዱበትን ሁኔታና መጠን በየጊዜው በመመዝገብ ለብሄራዊ ባንክ አጠቃላይ ሪፖርት እንዲያቀቡ መደረጉ ይታወሳል።

በሃገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ መንግስት በቅርቡ ወደ ሃገሪቱ የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የያዙትን የውጭ ምንዛሪ እንዲሁም የተለያዩ ጌጣጌጦች እንዲያስመዘግቡ ተጨማሪ መመሪያ መውጣቱን መዘገባችን ይታወሳል።

ይኸው መመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ከሚጓዙ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ አዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ለመሸጋገሪያነት የሚጠቀሙ መንገደኞችን ሁሉ የሚመለከት እንደሆነ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በዚሁ መመሪያ መንግስት የውጭ ምንዛሪያቸውን አስመዝግበው ወደ ሃገሪቱ የገቡ መንገደኞች ከሃገር ሲወጡ ያስመዘገቡትን የገንዘብ መጠን የት እንደቀየሩ ለመቆጣጠር ያለመ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።

ገንዘባቸው ተመዝግቦ ወደ ሃገሪቱ የገቡ መንገደኞች በተለይ ኢትዮጵያውያን ይዘው የገቡትን ገንዘብ በባንክ ብቻ እንዲመነዝሩ መመሪያው ቁጥጥር ማድረጉን ለመረዳት ተችሏል።

የብሄራዊ ባንክ ሃላፊዎች ከወራት በፊት ጥቁር ገበያ እየተባለ በሚጠራው መንገድ የሚካሄድ የውጭ ምንዛሪን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዕርምጃዎች ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በዚሁ መመሪያ መሰረት ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪን ይዘው ከሃገሪቱ ለመውጣት ከሞከሩ ኢትዮጵያውያን በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።

ይሁንና ባለስልጣናት መንገደኞች ወደ ሃገሪቱ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ መያዝ እንዳለባቸው የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።

በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ከፍተኛ ልዩነት ማሳየቱንና ድርጊቱ ለመንግስት ከፍተኛ ፈተና መሆኑን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።