የገበያ ማዕከል ለመገንባት ከ10 አመት በፊት ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ በዝግ ሂሳብ ያስቀመጡ ነጋዴዎች ጉዳዩ ሳይፈጸምላቸው በመቅረቱ ቅሬታ አቀረቡ

ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ የገበያ ማዕከላት ለመገንባት የሚያስችል መሬት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸው ከ580 ሚሊዮን ብር በላይ በዝግ ሂሳብ ያስቀመጡ ከ10ሺ በላይ ነጋዴዎች ቃል የተገባልን ሳይፈጸም 10 አመታት አስቆጠረ ሲሉ ቅሬታን አቀረቡ።

በአስሩም ክፍለ ከተሞች የገበያ ማዕከላት ለመገንባት በከተማው አስተዳደር ቃል ተገብቶላቸው እንደነበር የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በዝግ ሂሳብ ያስቀመጡት 583 ሚሊዮን ብር በባንክ ከገባ 10 አመት እንደሞላው አስታውቀዋል። የተገባልን ቃል ለ10 አመታት ችላ መባሉ አማሮናል ሲሉ የገለጹት ወደ 10ሺ አካባቢ የሚጠጉ ነጋዴዎች 110 አክሲዮን ማህበራት ተደራጅተው መቆየታቸውንም ለሪፖርተር ጋዜጣ አስረድተዋል።

ነጋዴዎቹ ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀረቡ ሲሆን፣ የሚገባቸውን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግርና መጉላላት መዳረጋቸውንም ተናግረዋል።

የአክሲዮን ማህበራቱ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ዘውዱ ግዛው ገንዘባቸውን በዝግ ሂሳብ አስቀምጠው የሚገኙ ነጋዴዎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

የከተማው አስተዳደር በበኩሉ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ መሰረት መሬት በድርድር መቆሙንና ለአልሚዎች እየቀረበ የሚገኘው በመደበኛና በልዩ ጨረታ ብቻ መሆኑን ምላሽ ሰጥቷል።

ይሁንና ከ10 አመት በፊት ቃል ተገብቶላቸው የነበሩት ነጋዴዎች የመሬት ጥያቄያቸው ከአዋጁ መውጣት በፊት መቅረቡን በመግለጽ ሊስተናገድ እንደሚገባ ጠይቀዋል። የከተማ አስተዳደሩ በተከታታይ እያወጣ ባለው የመሬት ጨረታ ለአንድ ካሬ መሬት ከ20 ሺ ብር በላይ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

የከተማ አስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመት ቢሮ ሃላፊ የሆኑት አቶ ለአለም ተሰራ በአሁኑ ወቅት የሊዝ አዋጅ እንዲሻሻል ተወስኗል በማለት የነጋዴዎቹ ጥያቄ ጉዳይ ይካተት አይካተት በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የሚታይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ይሁንና የሊዝ አዋጁ መቼ ማሻሻያ ተደርጎበት ወደ ስራ እንደሚገባ የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።