የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ አማጽያንን ማሰራቸው ተዘገበ

ግንቦት ፩ ( አንድ ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው የደቡብ ሱዳን የደህንነት ባለሥልጣናት ጁባ ውስጥ የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር አባላት እንደሆኑ የሚታመኑ ስድስት አማጽያንን አስረዋል።
ኢትዮጵያውያን አማጽያኑ የታሰሩት የአካባቢው ሚሊሻዎች ከሚጠቀሙባቸው ህገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ ለኢትዮጵያ መንግስት እጃቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር መሪ ጄነራል ቶዋት ፓል ቾይ የድርጅቱ ቃል አቀባይ በሆኑት በኮሎኔል ፓል ኦጅሉ ላይ “ በአማጽያኑ መታሰር ላይ እጃቸው አለበት” በማለት ክስ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር ለረዥም ዓመታት የህወኃት ኢሃዴግን መንግስት ሲዋጋ ከቆዬ በኋላ፤ በጁባው መንግስት አደራዳሪነት መሪው ፓል ቾይ እና ተከታዮቻቸው ለኢህአዴግ እጃቸውን ሰጥተው አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።
ይሁንና ቃል አቀባዩ አቶ ኦጅሉ በፓል ቾይ የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለውታል።ይልቁን የግንባሩን መሪ ፓል ቾይ የአማጽያኑን አመራር ካውንስል ሳያሳውቁ ድርጅቱንና ተዋጊ ኃይሉን በመክዳት ለኢትዮጵያ መንግስት እጃቸውን የሰጡ ከሀዲ ናቸው በማለት ቃል አቀባዩ ከሰዋል።እንደ ቃል አቀባዩ አቶ ኡጅሉ ገለጻ በደቡብ ሱዳን የሚገኘው ድርጅታቸው በሀገሪቱ መንግስት ድጋፍ እየተደረገለት ይገኛል። ይሁንና ጥቂት የቡድናቸው አማእያን ከደቡብ ሱዳን ኃይሎች ጋር ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ጥፋተኞች ሆነው በመገኘታቸው መታሰራቸውን አምነዋል።
ለመታሰራቸውም ዋነኛው ምክንያት የደቡብ ሱዳን መንግስት ባላወቀበት ሁኔታ ከተራቡ የማቲያንግ አኒዮር ሚሊሻዎች ጠመንጃ በመግዛታቸው እንደሆነ መናገራቸውን የሱዳን ትሪቢዩን ዘገባ ያመለክታል።
የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት እስካሁን ጉዳዩን አስመልክቶ ምንም ዓይነት አስተያዬት አልሰጡም።”